Monday, July 30, 2018

‹‹ከእኔ ክስና እስራት በስተጀርባ በመንግሥት ውስጥ ጡንቻቸው የጠነከረ ማፊያዎች ነበሩ››



አቶ መላኩ ፈንታ፣ የቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር


የዛሬው የቆይታ አምድ እንግዳ አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው፡፡ 50 ዓመት ጎልማሳው አቶ መላኩ 1981 .. ጀምሮ እስከ 2005 ድረስ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ከጀማሪ ኤክስፐርትነት እስከ ሚኒስትርነት ባሉ ኃላፊነቶች ከመሥራታቸው በተጨማሪ፣ በሠሩባቸውና በመሯቸው ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ በማምጣት የተመሠከረላቸው ናቸው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን በሚኒስትር ማዕረግ በዋና ዳይሬክተርነት መምራታቸው ይታወሳል፡፡ 2005 .. ግንቦት ወር ጀምሮ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረውና ክስ ተመሥርቶባቸው ለአምስት ዓመታት እስከ ግንቦት ወር 2010 .. ድረስ ታስረው ቆይተዋል፡፡ በቂ መረጃ ሳይሰበስብ ከሁለት ወይም ከሦስት ክሶች መብለጥ የሌለባቸውን ክሶች አብዝቶ በመክሰስ ዜጎችን ለእስር መዳረግ ተገቢ አለመሆኑን፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ ዜጎች ያለ ወንጀላቸው በወንጀል ተፈርጀው መታሰራቸው የፖለቲካ ምኅዳሩን ከማጥበብና ሰላምን ከማደፍረስ የዘለለ ሚና እንደሌለው መንግሥት ገልጾ፣ የበርካታ እስረኞች ክስ እንዲቋረጥና በይቅርታ እንዲፈቱ ሲያደርግ ለመጨረሻ የቅጣት ውሳኔ የተቀጠሩት አቶ መላኩም ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ተፈትተዋል፡፡ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት የሆኑትን አቶ መላኩ በትምህርት፣ በሥራ፣ በእስር ስላሳለፏቸው ጊዜያትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን እንሆ።


ሪፖርተር፡- የት ተወልደው እንዳደጉና የትምህርትዎን ሁኔታ ቢነግሩን?

አቶ መላኩ፡- ትውልዴም ዕድገቴም በጎንደር ከተማ ቀበሌ 09 ልዩ ስሙ ፒያሳ መድኃኔዓለም በሚባል አካባቢ ነው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቴን ኅብረት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በፋሲለደስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቅቄያለሁ፡፡ የመጀመርያ ዲግሪዬን ከአስመራ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ አግኝቻለሁ፡፡ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሬዬን አግኝቻለሁ፡፡ ስዊድን ከሚገኘው ራስመስብሮሞስ ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ ማኔጅመንትና በከተማ አስተዳደርም ሁለተኛ ዲግሪዬን ሠርቻለሁ፡፡ እንዲሁም በረቨኑ አድሚኒስትሬሽን ከካንቤራ (አውስትራሊያ) ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ አግኝቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራ የጀመሩት መቼና የት ነው?

አቶ መላኩ፡- ወደ ሥራ ዓለም የገባሁት 1981 .. በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ተሃድሶ ድርጅት በሚባል ተቋም ነው፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ ከጀማሪ ኤክስፐርትነት እስከ ፕላንና ፕሮግራም ኃላፊነት ድረስ ሠርቻለሁ፡፡ እዚያው ተቋም ውስጥ እያለሁ የደርግ መንግሥት ወድቆ ኢሕአዴግ አገሪቱን መምራት ጀምሮ ነበር፡፡ በወቅቱ ከተየተቋማቱ አቅም ያላቸው ሠራተኞች ተመርጠው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሲወሰዱ እኔም ተመርጬ ተወስጃለሁ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከከፍተኛ ኤክስፐርትነት እስከ አፋር ዴስክ ኃላፊነት ሠርቻለሁ፡፡ በዚህ ወቅት ትልቁ ሥራችን በልማት ወደ ኋላ ለቀሩ ክልሎች ድጋፍ መስጠት ነበር፡፡ ክልሎቹም አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌና ቤንሻንጉል ጉምዝ ነበሩ፡፡ ለእነዚህ ክልሎች የተለያዩ ድጋፎችን እንሰጥ ነበር፡፡ በዋነኛነት በዕቅድ ዝግጅት፣ በፕሮጀክት ክትትልና ድጋፍ፣ በመንግሥት መዋቅሮች ማለትም የፌዴራል ሥርዓቱን ለማጠናከር የሚከናወኑ ሥራዎችንና ከግጭት አፈታት ጋር የተለያዩ ሥራዎችን እንሠራ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የአፋርን ዴስክ የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶኝ ለብዙ ጊዜ እዚያ ሠርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡-  እርስዎ እንዴት የአፋር ክልልን በሚመለከት ሊሠሩ ተመደቡ? የክልሉ ተወላጆችን መመደብ ያልተቻለበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ መላኩ፡- ስለከተማ ካወራን በወቅቱ የሚታወቀው ዱፍቲ ብቻ ነው፡፡ የአሰብን መንገድ ተከትሎ ያሉ ከተሞች ካልሆኑ በስተቀር የአፋር ከተሞች የመስተዳድር አካላት አልነበሩም፡፡ ተወላጁም በትምህርት ላይ የሚገኝበት ወቅት አልነበረም፡፡ ተወላጁን ወደ ትምህርት ማስገባት፣ መዋቅሩን እስከ ወረዳ ድረስ መዘርጋትና የከተማ ማዕከሎችን መገንባት (ሰመራን ጨምሮ) እና ወደ ልማት ለመግባት የሚያስችሉ ሥራዎችን ከተባባሪዎች ጋር ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ሌላው የክልል ጉዳይ ዘርፍ የሚባለው፣ በሚኒስቴር ደረጃ ተዋቅሮ እንዲወጣ ማለትም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተብሎ ተዋቅሮ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ፣ ከዳይሬክተርነት ጀምሮ እስከ ሚኒስትር ዴኤታነት አገልግያለሁ፡፡ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሲዋቀር ከተማ ልማትን ጨምሮ ነበር የተዋቀረው፡፡ ስለዚህ በከተማ ደረጃ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች ሪፎርም ሲካሄድ፣ የጥናት ኮሚቴ አባል ሆኜም ሠርቻለሁ፡፡ እኔ ወደ ሥልጣን በመጣሁበት ወቅት በክልሎች ግጭቶች ተፈጥረው ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ግጭቶቹ በየትኞቹ ክልሎች ነበር የተፈጠሩት?

አቶ መላኩ፡- በጋምቤላ ግጭት ተከስቶ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ሲወሰን (1996 ..) ቡድኑን ይዤ ወደ ክልል የሄድኩት እኔ ነኝ፡፡ ትልቁን ሥራ ሰንሠራ የነበረው ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስ ነበር፡፡ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ ሱዳን ተሰደው ነበር፡፡ በርካታ ቤቶችም ተቃጥለው ነበር፡፡ በርካታ የልማት አውታሮችም ወድመው ነበር፡፡ ከሕዝቡ ጋር ውይይቶች አድርገን መግባባት ላይ ከደረስን በኋላ፣ ሁሉንም ችግሮች በመፍታት ወደ ነበሩበት ለመመለስ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ግጭቱ በአንድ ክልል ላይ በመሆኑ መነሻ ምክንያቱ ምን ነበር?

አቶ መላኩ፡- ግጭቱ በክልሉ ተወላጆችና ከሌላ ክልሎች በመጡ ነዋሪዎች መካከል ነበር፡፡ እርስ በርሳቸውም በአኝዋና በኑዌር መካከል ነበር፡፡ ሌላው የተሳተፍኩት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል በተነሳ ግጭት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ግጭትስ መነሻው ምን ነበር?

አቶ መላኩ፡- የእነሱ ግጭት የይገባኛል ጥያቄ ነበር፡፡ ይኼም በሪፈረንደም እንዲፈታ ሲወሰን እሱንም መርቻለሁ፡፡ ያኔ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ተግባራዊ ባለመደረጋቸው፣ አሁን ድረስ ስለግጭቶቹ በመገናኛ ብዙኃን ሲነገር እሰማለሁ፡፡ በእኔ እምነት ግጭቶቹ የሕዝብ አይደሉም፡፡ አመራሩ የሚፈጥረው ግጭት ነው፡፡ ይኼንን የምለው ብዙ መድረኮች ላይ በአፋር፣ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች በመገኘቴ ነው፡፡ በአፋርና በኢሳ ግጭት፣ እንዲሁም በሶማሌና በኦሮሚያ ግጭትም በሕዝብ መድረክ ላይ ተሳትፌያለሁ፡፡ ከመድረኮቹ እንደተረዳሁት በሕዝብ መካከል ምንም ዓይነት ግጭት የለም፡፡ ውይይት አድርገን ችግሩን ስንፈታ ተፈናቅለው ወደሌላ ቦታ ሄደው የነበሩት ሲመለሱ፣ ሕዝቡ በመላቀስና በመተቃቀፍ ያለውን ፍቅር ታያለህ፡፡ ሕዝቡ አብሮ ኖሯል፡፡ ተዋልዶ አብሮ አድጓል፡፡ ሌላውን አካባቢ አያውቀውም፡፡ አመራሩ ግን ይኼንን የአስተዳደር ሥልጣን ይዞ ለመቀጠል በማሰብ ‹‹መሬትህን ተነጥቀሀል›› ብሎ ሕዝቡን ይቀሰቅሳል፡፡ ዓላማው በሥልጣን ለመቆየትና ግጭት ሲፈጠር ደግሞ የመንግሥት ‹‹መጠባበቂያ በጀት›› የሚባል የማይወራረድና ለአመራሩ ሲሳይ የሆነ በጀት ስላለ ይኼንን ለመቀራመት፣ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለመመዝበር፣ እንዲሁም የኮንትሮባንድ ንግዱን ለማጧጧፍ የሚያስችል ዕድል ስለሚፈጥርለት አመራሩ ሥራዬ ብሎ ግጭቱ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ እስካሁን ግጭቶች የማይፈቱት አመራሩ በታማኝነት ስለማይሠራና በግጭቱ ተጠቃሚ በመሆኑ ነው፡፡

እኔ በአፋርና በኢሳ፣ በጋምቤላ ሕዝቦች፣ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች የተነሱ ግጭቶችን ከማየቴም በተጨማሪ፣ በውጭና በአገር ውስጥ ተቋማት ጥናት አስደርገን የሕዝብ ግጭት እንደሌለ ተረጋግጧል፡፡ በወቅቱ በሶማሌና በኦሮሚያ መካከል በተነሳ ግጭት፣ የሁለቱም ክልሎች ተደምሮ ይገቡናል ያሉት ከአንድ ሺሕ በላይ ቀበሌዎችን ነበር፡፡ የሶማሌ ክልል እስከ አዳማ ድረስ የይገባኛል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ኦሮሚያ ደግሞ እስከ ጅግጅጋ ድረስ የይገባኛል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕዝብ ዘንድ ወርደን አመራሩንም እያሳተፍን ባደረግነው ውይይት የልዩነት ቀበሌዎች 460 አይበልጡም ነበር፡፡ እስከማስታውሰው ድረስ በወቅቱ ከስምንት ቀበሌዎች ከሞያሌና ከአዋሽ አለፍ ብሎ የሚገኝ የጫት ቦታ በስተቀር፣ በሁሉም ላይ ሪፈረንደም አካሂደናል፡፡ ሁሉም ነገር በሰላምና በስምምነት ተጠናቋል፡፡ ነገር ግን የክልል መንግሥታት እንዲሠሩ የተቀመጡ የልማት አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ ግጦሽ በጋራ የሚጠቀሙበት ትምህርት ቤትና ክሊኒኮች በጋራ የሚጠቀሙበት ዕቅዶች ነበሩ፡፡ ግን በአመራሮቹ አልተሠሩም፡፡ ኢትዮጵያ አንድ አገር ናት፡፡ እንደ አንድ አገር ካላሰብናት ለራስ ጥቅም ሲባል ‹‹መሬትህን ተነጥቀሀል›› እያለ አመራሩ የሚቀሰቅሰው ከሆነ፣ ችግሩ መቼም አይፈታም፡፡ አንድ አገር መሆኗን አምኖ የአስተዳደር ወሰኑን ለማስተዳደርና የልማት አቅርቦቱን ለማስተካከል ብቻ መካለሉን አውቆ መሥራት ብቻ ነው ሰላም ፈጥሮ አንድ ላይ መኖር የሚያስችለው፡፡ በጋራ የሚለሙ የግጦሽ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የውኃ ልማቶች ተለይተው ተሰጥተዋቸው ነበር፡፡ ግን አመራሩ ሊሠራው ፈቃደኛ ባለመሆኑ አንዱም አልተሠራም፡፡ እኔም 1997 .. ወደ ገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆኜ በመዛወሬ፣ በዕቅድ ያስቀመጥናቸው ስምምነቶች የት እንደደረሱ ማወቅ አልቻልኩም፡፡ ባለመተግበራቸው ግን ግጭቱ እስካሁን ቀጥሏል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ እንደነገሩን በተለይ የሶማሌና የኦሮሚያ ግጭት ረዘም ያሉ ዓመታትን አስቆጥሯል፣ አሁንም በተባባሰ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) ወደ ክልሎቹ ሄደው ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ የሁለቱን ክልሎች መሪዎች በማጨባበጥ ችግሩ መፈታቱንና አመራሮቹ የበለጠ ችግሩን የሚፈቱበት አቅጣጫ አስቀምጠው ነበር፡፡ ነገር ግን ግጭቱ በከፋ ሁኔታ በመቀጠሉ መከላከያና ፌዴራል ፖሊስ ጣልቃ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ ለግጭቱ መቀጠል ተጠያቂ መሆን ያለበት አመራሩ ብቻ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ መላኩ፡- አመራሩ ቁርጠኛ ከሆነ የማይፈታ ነገር የለም፡፡ አንድ ምሳሌ ልንገርህ፡፡ የሶማሌንና የኦሮሚያን ግጭት ለመፍታት በምሠራበት ወቅት፣ ቀን ከእኛ ጋር አመራሩ ተሰብስቦ ለሕዝቡ መነገር ያለበትን መልዕክት እንዲያስተላልፍ ተስማምተን እንለያያለን፡፡ ነገር ግን ማታ ለሕዝቡ ወደታች የሚተላለፈው ሌላ ነገር ነው፡፡ ግጭትን የሚያፋፍም ነገር ለሕዝቡ ይነግሩታል፡፡ በአንድ ወቅት እርስ በርስ በሚጋጩበት ጊዜ ከሁለቱም ክልሎች ፖሊሶች ሞተው ተገኙ፡፡ ስለዚህ የክልሉ ፖሊስ በግጭቱ እየተሳተፈ ነበር ማለት ነው፡፡ አመራሮች ግን ግጭቱ የሕዝብ መሆኑን ነበር የሚናገሩት፡፡ ከጀርባ ድጋፍ የሚሰጠው ግን ፖሊስ ነበር፡፡ የመከላከያና የደኅንነት ሠራተኞች መረጃቸውን ለእኔ ሰጥተው ነበር፡፡ መድረክ ላይ ቢያወጡት ሊጠቁ እንደሚችሉ ሥጋት ስለነበረባቸው መረጃቸውን ሰጥተውኛል፡፡ ምክንያቱም በስብሰባችን ላይ የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ የፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተርና የክልሎች አመራሮች ስለነበሩ እነሱን በመፍራት ነው፡፡ ይኼ የሚያሳየው የአመራር ችግር መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ሥራው ሊሠራ እንደማይችል ስለገባኝ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሪፖርት አቀረብኩ፡፡ እሳቸውም ሪፖርቱን ካዩ በኋላ፣ ‹‹ይኼ የአመራሩ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖር ችግር ነው›› በማለት ራሳቸው የክልሎቹ ፕሬዚዳንቶች ወርደው እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ በወቅቱ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶና የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲል ጀብሪል መመርያው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሰጣቸው በኋላ፣ እኛ በድጋሚ ሄደን ስንሠራ መልክ እየያዘ መጥቶ ነበር፡፡

ይኼ የሚያሳየው ከላይ እስከ ታች አመራሩ ‹‹የእኔ ሥራ ነው›› ብሎ ከያዘው የሚፈታ ችግር መሆኑን ነው፡፡ ችግር መፍታት ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰቡን የልማት አጀንዳ መመለስ ከተቻለ ወደ ግጭት የሚያስኬድ ጥያቄ የለም፡፡ የኅብረተሰቡና የወጣቱ ትልቅ ችግር የእኩልነትና የእኩል ተጠቃሚነት ጉዳይ ነው፡፡ የተወሰነ ሀብታምና በርካታ ደሃ በሚኖርበት አገር አመራሩ የግጭት መንገድ ከከፈተለት ግጭቱ እየቀጠለ ይሄዳል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትዕዛዝ በተመለከተ ግጭት ሲያጋጥም በክልሉ መንግሥት መፈታት ካልቻለ መከላከያም ሆነ ፌዴራል ፖሊስ ጣልቃ እንዲገቡ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ግጭት ለማብረድ የመጀመርያው ዕርምጃ የፀጥታ ኃይሉን ማሰማራት ነው፡፡ የተፈናቀሉትን ወደ ቦታቸው መመለስ፣ የወደመ ንብረትና የልማት አውታር ካለ ማስተካከልና ሰላም ማስፈን የአጭር ጊዜ ዕቅድ መሆን አለበት፡፡ አስፈላጊም ነው፡፡ ነገር ግን ዘለዓለም ወታደር ማቆም መፍትሔ አይሆንም፡፡ ጎን ለጎን የረዥም ጊዜ ዕቅድ ሊኖር ይገባል፡፡ መሠረታዊ የሆነውን የሕዝቡን ችግር በማወቅና በመለየትም መፍታት ያስፈልጋል፡፡ በግጭት ውስጥ ለጊዜው አትራፊዎች ስለሚኖሩ፣ እነሱንም በመለየት መማር የሚያስፈልገውን አስተምሮ መመለስ፣ ሊማር የማይችለውን ደግሞ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ግጭት ሲፈታ ግጭቱን ከማረጋጋት አንስቶ እስከ ዘላቂ ሒደቱ ድረስ አገናኝቶ መሥራት ካልተቻለ ወታደር ማስገባት ለጊዜው ቢያቆመውም ተመልሶ መቀስቀሱ አይቀርም፡፡ ወታደሩ ሲወጣ ተመልሶ ይቀሰቀሳል፡፡ ዘለዓለም ወታደር አቁመህ አትችልም፡፡ የግጭቱን መነሻ በደንብ አጥንቶ መፍትሔ መስጠትና ሒደቱን መከታተል አስፈላጊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በሚኒስትር ማዕረግ ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት መቼ ነበር?

አቶ መላኩ፡-  የገቢዎች ሚኒስትር ሆኜ የተሾምኩት 1997 .. አገራዊ ምርጫ በኋላ 1998 .. አዲሱ መንግሥት ሲዋቀር ነው፡፡ በወቅቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጉምሩክንና ብሔራዊ ሎተሪን በበላይነት ይቆጣጠር ነበር፡፡ በወቅቱ አገርም በለውጥ ውስጥ ስለነበረች ትኩረታችን ቀደም ብለው በነበሩ ኃላፊዎች ተጀምረው በነበሩ የሪፎርም ሥራዎችን እያስኬድን መሠረታዊ የለውጥ ጥናቶችን ከተሻሉ አገሮች ልምድ በመውሰድና ተቋማቱን በማዋሀድ (ከብሔራዊ ሎተሪ በስተቀር) የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን 2000 .. አቋቋምን፡፡ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በመሆንም እስከታሰርኩበት ጊዜ ድረስ ሠርቻለሁ፡፡ ተቋሙ ገንዘብ ሰብሳቢ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ሰጪም ነው፡፡ ሕግ አስከባሪም ነው፡ ስለዚህ መሉ አቅም ያለው ተቋም መፍጠር አለብን በማለት መሠረታዊ የሆኑ የለውጥ መሣሪያዎችን በመጠቀም ለመሥራት ሞክረናል፡፡ ሪፎርሙን በመሥራታችንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ አምጥተናል፡፡ በወቅቱ ትምህርት ሚኒስቴር በዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡትን ወስዶ ከጨረሰ በኋላ (3.5 በላይ ውጤት ያስመዘገቡትን ለመምህርነት ይወስድ ነበር) ውጤታማ ተመራቂዎችን ወስደን እያሠለጠንን ተቋሙ በዕውቀት እንዲመራ አድርገናል፡፡ በሲስተም መመራት ያለበት ተቋም ቢሆንም ይኼ በአገር ደረጃ ያልተለመደ በመሆኑና ትኩረት ባይሰጠውም እኛ ጀምረን ነበር፡፡ ተቋሙን ሞዴል ለማድረግ ግልፅ ስትራቴጂዎች አስቀምጠን ነበር ያቋቋምነው፡፡ እያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ ምን መሥራት እንዳለበት ስትራቴጂ አስቀምጠንና ዲዛይን ሠርተን ወደ ትግበራ በመግባታችን ስንጀምር የነበረው ሰባት ቢሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ የነበረ ቢሆንም፣ በታሰርንበት ወቅት 85 ቢሊዮን ብር አድርሰነው ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡-  የንግዱ ማኅበረሰብ ወደ ታክስ ሲስተም እንዲገባ በማድረግ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ያደረጉት እርስዎ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ አበርክቻለሁ የሚሉትን አስተዋፅኦ ቢነግሩን?

አቶ መላኩ፡- እኔ በበኩሌ አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ፡፡ ሌሎችም የተቋሙ ሠራተኞችም የየራሳቸው አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊ አስተዋፅኦም ከፍተኛ ነበር፡፡ የእሳቸው አስተዋፅኦ የፖለቲካ አስተዋፅኦ ነው፡፡ ተቋሙን ሪፎርም ከማድረጋችን በፊት ከእሳቸው ጋር ብዙ ውይይት አድርገናል፡፡ ተቋሙ ውጤታማ የሚሆንበትን መንገድ ካጠናሁ በኋላ ሪፎርሙን ለመጀመር የእሳቸውን ድጋፍ ማግኘት ነበረብኝ፡፡ ሦስት አማራጮችን አስቀመጥኩላቸው፡፡ የመጀመርያው አማራጭ ሲስተም መፍጠር ሳያስፈልግ ፕሮቶኮል ጠብቆ በየስብሰባውና በየኮክቴል ሚኒስትር ሆኖ መገኘት፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኅብረተሰቡ እንደሚያስበው ‹‹ሲሾም ያልበላ›› ዓይነት አስተሳሰብ ይዞ የድርሻን እየወሰዱ መኖር የሚል ሲሆን፣ ሦስተኛው ግን የእሳቸውን ድጋፍ የሚፈልገው ከሁሉም ጋር ተቆራርጦ ለውጥ ማምጣት የሚሉ አማራጮች ነበሩ፡፡ እኔ የምመርጠው ሦስተኛውን እንደሆነ ስነግራቸው ‹‹ያየሃቸው አማራጮች ትክክል ናቸው፡፡ የመረጥከውም የእኔም ምርጫ ነው፡፡ በመሆኑም ሙሉ ድጋፍ እስጥሀለሁ፤›› አሉኝ፡፡ በመሆኑ ውጤታማ ሆነናል፡፡ ባይሆን ኖሮ፣ በሲስተም እንዲመራ የማይፈልጉ አካላት እንደፈለጉ ለማዘዝ ጣልቃ ይገቡ ነበር፡፡ አቶ መለስ ለሥራ አስፈጻሚው ‹‹አማላጅነታችሁን ትታችሁ ሥራችሁን ሥሩ፡፡ በዚህ ተቋም ውስጥ ጣልቃ መግባት አትችሉም፡፡ መደገፍ ባችችሉም አማላጅ መሆናችሁን አቁሙ፤›› በማለታቸው አንድም ሰው ጣልቃ አይገባብንም ነበር፡፡ አማራጭ ያስቀመጥኩት ደግሞ እንደ ማንም እጄን ተጠምዝዤ መሥራት ስለማልፈልግ ነው፡፡ የተለመደው ግን አሉባልታና ወሬ ነበር፡፡ የእኛንም ክሶች ካየሃቸው በባህሪያቸው አሉባልታዎች ናቸው፡፡ ሁለም አደብ ገዝቶ ቆይቶ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የመሳፍንት ዓይነት አስተሳሰብ ይዞ ጣልቃ ለመግባት ሞከረ፡፡ ያንን አይሆንም በማለቴ የእስር ሰለባ ለመሆን ችለናል፡፡ አንድ ቦታ ላይ ሥልጣን ሲሰጥህ በግልህ ልትገለገልበት ሳይሆን፣ ባለህ አቅም ሕዝብንና አገርን እንድታገለግልበት ነው፡፡ ቸርችል በአንድ ወቅት ሲናገር ‹‹እንግሊዝ ለሺሕ ዓመታት ብትጥር በእኔ ጊዜ የተሠራውን ያህል አላየንም፤›› ይል ነበር፡፡ ይኼ ማለት ሊሠራ ያሰበው ራዕዩ ትልቅ ተቋም ለመፍጠር ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ራዕይ ማሰብ አለብህ፡፡ እንደዚያ ካሰብክ አንድ ተቋም ሳይሆን ብዙ ልትቀይር ትችላለህ፡፡ እኔ ሥልጣኔን ለክብር አልተጠቀምኩበትም፡፡ በድሮ ኑሮዬ ላይ የመመካት ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም አወጣጤን አውቀዋለሁ፡፡ ሥልጣን ደግሞ ርስት ባለመሆኑ እንደምወርድ ስለማውቀው ከሕዝብ አልራቅሁም፡፡   

ሪፖርተር፡- በግንቦት ወር 2005 .. በመጀመርያዎቹ ቀናት በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከሥራ ባልደረባዎችዎ ጭምር በቁጥጥር ሥር ውላችሁ  ለአምስት ዓመታት በእስር ላይ ቆይተዋል፡፡ እስኪ ስለአጠቃላይ ሁኔታው ይንገሩን?

አቶ መላኩ፡- ከመያዜ ከጥቂት ቀናት በፊት በባህርዳር የድርጅት ስብሰባ ላይ ቆይቼ ግንቦት 2 ቀን 2010 .. ነው ወደ አዲስ አበባ የተመለስኩት፡፡ አዲስ አበባ የገባሁት ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ ስለነበር ወደ ቤቴ ገብቼ ልብሴን ከየቀርኩ በኋላ፣  ከቀትር በኋላ ቢሮዬ ሥራ ላይ ነበርኩ፡፡ ወታደሮች ቢሮዬ መጥተው በሙስና መጠርጠሬን ነግረውኝ የያዙትን የመያዣ ወረቀት አሳይተው ‹‹ይፈለጋሉ›› አሉኝ፡፡ ስንት ሌባ ባለበት አገር እኔን ሌባ ካለችሁኝ ምን አደርጋለሁ? የምትፈልጉትን አድርጉ አልኳቸው፡፡ ቢሮዬን ሲፈትሹ ቆዩና ሠራተኛ በሚወጣበት 11 ሰዓት ላይ ከቢሮዬ ወደ ምድር ይዘውኝ ወረዱ፡፡ በወቅቱ የነበረውን ሠራዊት ለተመለከተ ከባድ አሸባሪ ድርጅት ለመቆጣጠር እንኳን ያንን ያህል ሠራዊት አይሰማራም፡፡ እኔ ‹‹›› ቢሉኝ የፈለጉበት ድረስ ሄጄ እጄን ለመስጠት የሚያሰጋኝም ሆነ የሚያስፈራኝ ሥራ ስላልሠራሁ ችግር አልነበረብኝም፡፡ ከዚያም አመሻሽ ላይ 1230  ሰዓት ሲሆን ወደ መኖሪያ ቤቴ ይዘውኝ ሄዱ፡፡ በመኖሪያ ቤቴ እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ድረስ የሚችሉትን ያህል ሲበረብሩ አመሹ፡፡ በሕጉ ግን ብርበራም ሆነ ፍተሻ የሚደረገው እስከ 12 ሰዓት ድረስ ብቻ መሆኑ ተደንግጎ ቢገኝም፣ በእኔ ላይ የተደረገው ግን ሕግን የጣሰ ተግባር ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር በቤቴ ውስጥ በብርበራው ምንም ነገር ማጣታቸውን እየተደዋወሉ ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ ልብሴን መቁጠር ጀመሩ፡፡ ሲጨርሱ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ወሰዱኝ፡፡ እዚያም ሦስት ወር ከአሥር ቀናት ‹‹ሳይቤሪያ›› በሚባለው ዙሪያውን ግንብ በሆነ ቀዝቃዛ ጭለማ ቤት አንድቆይ ተደረገ፡፡

ሪፖርተር፡- በማዕከላዊ ሌሎች የማሰሪያ ክፍሎች አሉ? ሌሎቹ ከሳይቤሪያ በምንድነው የሚለዩት? በሳይቤሪያ ማሰሪያ ክፍል ከእርስዎ ጋር የታሰሩ ነበሩ?

አቶ መላኩ፡- ሳይቤሪያ ውስጥ የታሰርኩት ብቻዬን ነው፡፡ 15 ደቂቃ ብቻ ፀሐይ ለመሞቅ ይከፈትሃል፡፡ ሳይቤሪያን ጨምሮ አራት ማሰሪያ (ማሰቃያ ማለት ይቀላል) ክፍሎች አሉ፡፡ ሁለተኛው ጣውላ ቤት ይባላል፡፡ ቀን ተከፍቶ ይውላል፡፡ ሦስተኛው ጭለማ ቤት ሲሆን፣ ከሳይቤሪያ የሚለየው ቅዝቃዜው ቀነስ ያለ ነው፡፡ በቀን 15 ደቂቃ ለፀሐይ ተብሎ ከመከፈቱ በስተቀር ተዘግቶ ይውላል፡፡ ከሁሉም የተሻለው ‹‹ሸራተን›› የሚባለው ማሰሪያ ነው፡፡ ሌሎቹን ሒደቶች አልፎ በድብደባና በተለያዩ ስቃዮች ውስጥ አልፎ ምስክር ለመሆን የተስማማና ምርመራውን ያጠናቀቀ የሚታሰርበት የተሻለ የሚባለው ነው፡፡ ክፍት ሆኖ ስለሚውል መዟዟር ይቻላል፡፡ ሳይቤሪያ ስትታሰር ቤተሰብ የሚያመጣልህን ምግብ እነሱ ተቀብለው ይሰጡሀል እንጂ ከማንም ጋር አትገናኝም፡፡ እኔም ቤተሰቦቼን ያገኘኋቸው በመጀመርያው ሳምንት የተወሰኑ ቀናት ብቻ ነው፡፡ ለመፀዳዳት እንኳን የሚፈቀድልህ ጠዋት 12 ሰዓትና ማታ 12 ሰዓት ብቻ ነው፡፡ እኔ ለመፀዳዳት ስወጣ የሁሉም ማሰሪያ ክፍሎች በሮች ይዘጋሉ፡፡ ሰው እንዳያገኘኝ ይሁን ወይም እንዳያየኝ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ምርመራ የሚደረግብዎ በስንት ሰዓት ነው? ቀን ሙሉ ነው ወይስ ሌሊቱን?

አቶ መላኩ፡- ምርመራ የሚያደርጉት በአብዛኛው ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ነው፡፡ እኔን ለምርመራ ብዙ አልጠሩኝም፡፡ ወሬ ከለቃቀሙ በኋላ ያንን ወሬ እውነት ውሸት መሆኑን ለመጠየቅ ይጠሩኛል፡፡ ሌላው ግን ማታ ሲመላለሱ እሰማለሁ፡፡ ሕጉ የሚያዘው ምርመራ በቀን እንዲደረግ ቢሆንም፣ በማዕከላዊ ግን ሌሊት ነው፡፡ ድብደባን ያካተተ ምርመራ በመሆኑ ሌሊት ይካሄዳል፡፡ አያያዙን በሚመለከት እውነት የሰው ልጅ በሰው ላይ ይጨክናል ወይ? የሚለውን ጭካኔ የተመላበት ድርጊት የምታይበት ነው፡፡ ተመርማሪዎቹ የሚያልፉት እኔ በታሰርኩበት በር ሥር ስለነበር ሲያመላልሷቸው ይሰማኝ ነበር፡፡ ለፀሐይ በምወጣበት ሰዓትም የተመቱ ሰዎችን የሰውነት ጉዳት አይቻለሁ፡፡ ፍርድ ቤትም ‹‹ተደብድበናል›› ብለው ሰውነታቸውን ሲያሳዩም ተመልክቻለሁ፡፡ እዚህ ላይ የሚገርመው ነገር የተደበደበ ገላን የተመለከተው ፍርድ ቤት ምንም ሳይል ያልፍ ነበር፡፡ ለጊዜ ቀጠሮ ስሄድም አብረውኝ በሰንሰለት የሚታሰሩ ይነግሩኛል፡፡ አያለሁም፡፡ አንዳንድ ጊዜም ማታ ማታ ለምርመራ ተጠርቼ ስሄድ፣ ከምርመራ ክፍሉ ጎን ባሉ ክፍሎች ሲደበደቡና ሲጮሁ ሰምቻለሁ፡፡ በእርግጥ እኔ ተዘግቶብኝ ከመቀመጥ ውጪ ድብደባ አልደረሰብኝም፡፡ የጤና ችግር ቢኖርብኝም ፖሊስ ሆስፒታል ይወስዱኝና ጉሉኮስ እንዳገኝ ያደርጉኛል፡፡ ተጨማሪ ምርመራና መድኃኒት ስጠይቅ ‹‹ከጉሉኮስ ያለፈ መድኃኒት እንዳትሰጡት ተብለናል›› ይሉኛል፡፡

አንድን አመራር ‹‹እንዴት በድብደባ ምርመራ ታደርጋላችሁ?›› ብዬ ጠይቄው ነበር፡፡ ድብደባው ‹‹ሚስጥር አውጣና ምስክር ሁነን›› ነው፡፡ ምስክር እሆናለሁ ያለ የሐሰት ምስክርነት ቃላት ይዘጋጁለትና እንዲያጠና ይደረጋል፡፡ አልመሰክርም፣ አላምንም ላለው ደግሞ የሐሰት ክስ ይዘጋጅለታል፡፡ የጠየቅሁት አመራር የሰጠኝ ምላሽ ‹‹የሽብር ተጠርጣሪን ለማሳመን ከዚህ የተሻለ መንገድ የለንም፡፡፡ ሙስናን በሚመለከት ከዚህ በፊት ድብደባ የለም ነበር፡፡ እናንተን በሚመለከት ከዚህ በፊት ድብደባ የለም ነበር፡፡ እናንተን ጨምሮ ካሁን በኋላ የሚመጡትን እንድንደበድብ ትዕዛዝ ተሰጥቶናል፤›› አለኝ፡፡ ‹‹ለመጀመርያ ጊዜ በእናንተ ላይ ድብደባ እንድንጀምር ተነግሮናል፤›› ብሎኛል፡፡ አሁን አሁን አመራሮቹ በቴሌቪዥን ‹‹ድብደባ የለም›› ብለው ሲናገሩ ስሰማ በጣም ይገርመኛል፣ ያሳዝነኛልም፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ሳይቀር እውነቱን እያወጣው ስለሆነ ተመሥገን ነው፡፡ ማዕከላዊ በደርግ ጊዜ ግፍና ደበል ሲፈጸምበት የነበረና የሰው ልጆች ከፍተኛ ስቃይ ሲያዩበት በመሆኑ፣ መዘጋት እንዳለበት መወሰኑን አቶ ኃይለ ማርያም ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን ደርግ ብቻ ሳይሆን ኢሕአዴግም ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጽምበት የነበረ፣ ከፍተኛ ኢሰብዓዊ ድርጊት ሲፈጸምበት የቆየ ለመሆኑ እኔ እራሴ ምስክር መሆን እችላለሁ፡፡ ጥፋትን አምኖ ይቅርታ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የእስርና የማሰቃያ ቦታን መቀየር ብቻ ሳይሆን አዕምሮንም መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ አዲስ ተቋም ተፈጠረ፣ ማዕከላዊ ተዘጋ ከተባለም በኋላ ቢሆን ማረሚያ ቤቶች ሄዶ ማየት ነው፡፡ የሰውነት ክፍላቸውን ያጡ ሞልተዋል፡፡ በመሆኑም መቀየር አስተሳሰብን ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  ከግንቦት 2 ቀን 2005 .. እስከ ጥቅምት  2006 .. ድረስ በማዕከላዊ ቆይታችሁ በሦስት መዝገቦች (የመዝገብ ቁጥር 141352141354 እና 141356) ክስ ተዘጋጅቶ ቀርቦባችኋል፡፡ በሦስቱም የክስ መዝገቦች እርስዎ ነበሩበት፡፡ የክሶቹን መብዛትና አጠቃላይ ይዘታቸውን እንዴት አገኙት?

አቶ መላኩ፡- ወደ ክሶቹ ከመሄዴ በፊት ሒደቱ ምን ይመስላል? ክሱስ ለምን አስፈለገ? የሚለውን ማየት ተገቢ መስሎ ይታየኛል፡፡ ክሶቹ ሆን ተብለው ለርካሽ ፖለቲካ ወይም ቂም ለመወጣት የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ዓቃቤ ሕግም ሆነ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ያዘጋጁት ክስ አይደለም፡፡ ይኼንን የምልበት ምክንያት፣ ‹‹መላኩ ይታሰር›› ተብሎ የተወሰነው ወንጀል ሠርቷል ተብሎ በተከታተለው አካል ሳይሆን የተለየ ቡድን (ከከፍተኛ ቁልፍ የመንግሥት ባለሥልጣናት) ተደራጅቶ፣ በኮሚቴ ተወስኖና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቦ የእሳቸውን ይሁንታ ሲያገኝ ነው የታሰርኩት፡፡ የኮሚቴው ሁሉም አባላት ተስማምተውበት ሳይሆን በድምፅ ብልጫ በደኅንነት፣ በመከላከያ ሚኒስቴርና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የአብላጫ ድምፅ የተላለፈን ‹‹ይታሰር›› ትዕዛዝ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ ሳይነሱ በማፅደቃቸው ነው የታሰርኩት፡፡ ይኼ ከመነሻው የሕግ የበላይነትንና ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ነው፡፡ ሁለተኛውና የሚገርመው ነገር አንደ የድርጅት አባልና የሥራ አስፈጻሚ  ኮሚቴ አባል ከመታሰሩ በፊት ጉዳዩ ለድርጅት መቅረብ ነበረበት፡፡ እኔ ደግሞ ከመታሰሬ በፊት ቀደም ብሎ ‹‹ከሙስና የፀዳ›› ተብዬ ተገምግሜ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆኜ ነበር፡፡ የድርጅት አባል ከሆንኩበት 1992 .. ጀምሮ አንድም ቀን በሙስና ተገምግሜም ሆነ ጣት ተቀስሮብኝ አላውቅም፡፡ በእኔ ላይ የተነሳ ነጥብም ሆነ የቀረበ ጥናት የለም፡፡ ደኅንነት ሲከታተልና ሲያጠና ነው የሚውለው፣ ውሎዬ ይታወቃል፡፡ ሀብት ንብረቴ ይታወቃል፡፡ አለችን የምላት ቤትም ብትሆን በፀረ ሙስና የተመዘገበችና በድርጀትም የምትታወቅ ነች፡፡

የሥራ አስፈጻሚ አባል ከመታሰሩ በፊት በድርጅቱ መገምገም እንዳለበት የተቀመጠ አሠራር ቢኖርም በእኔ ላይ አልተደረገም፡፡ ለእኔ ችግር አይኖረው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከመጣሁበት ድርጅት ብአዴን ጥቂት የማፊያ ቡድኖች ንቀታቸውን በሚያሳይ ሁኔታ ነው ድርጊቱን የፈጸሙት፡፡ ከእነዚህ ጥቂት የማፊያ ቡድኖች ውጪ ሌላው የብአዴን አመራር መታሰሬን የሰማው በመገናኛ ብዙኃን ነው፡፡ ይኼ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ብአዴንን መናቅና ማዋረድ ጭምር ነው፡፡ መንግሥት ውስጥ የተፈጠረ ሌላ የማፊያ መንግሥት ነበር፡፡ እኔ ግለሰብ ነኝ፡፡ በፈለግኩት መንገድና ጊዜ ሊገድሉኝም ይችላሉ፡፡ ግን አንድን ማኅበረሰብ የወከለን ድርጅት በዚህ ደረጃ አውርደህ እንደ ሕዝብ የድርጅት አመራርን በመገናኛ ብዙኃን እንዲሰማ ማድረግ፣ የንቀቱና አምባገነንነቱ ጥግ የት ድረስ እንደሄደ የሚያሳይ ነው፡፡ ሌላው ‹‹ጥናት ተካሂዶ ነው የታሰሩት›› የተባለው ፀረ ሙስና ያጠናው ጥናት አይደለም፡፡ የደኅንነት አካሉ አጠናሁ ብሎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረበና በመገናኛ ብዙኃን ከተነገረ በኋላ ነው ጉዳዩ ወደ ፀረ ሙስና የተዛወረው፡፡ ለዚህም ነው እጅ እግር የሌለውና ውጥንቅጡ የወጣ ክስ የቀረበው፡፡ ቂም ይዞ የከረመውና በተለይ እመራው በነበረው ተቋም ውስጥ እንደፈለገ ማዘዝና ለሚቀርበው ነጋዴም ሆነ ግለሰብ የፈለገውን እንዲያገኝ ማድረግ ያልቻለው ጥቂት ቡድን፣ ከአራት የማይበልጡ ነባር ታጋይና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ‹‹መላኩ የፀጥታ ሥጋት ስለሆነ መታሰር አለበት›› የሚል ሐሳብ በኮሚቴ ወስነው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበው ነው እንድታሰር ያደረጉት፡፡ እኔ በምን መለኪያ ነው የፀጥታ ሥጋት የምሆነው? የታጠቀ ኃይል የለኝ፣ የምቀሰቅሰው ኃይልና መሣሪያ የለኝ፡፡ ሆን ተብሎ እኔን ለመጉዳት የተደረገ ሴራ ነው፡፡ አሉባልታን ክስ ማድረግ አይቻልም፡፡ ክስ መሆን የሚችለው በእውነተኛ ማስረጃ የተደገፈ ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው መጠየቅ ያለበት በሠራው ወንጀል ብቻ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚለው ይኼንኑ ነው፡፡

የእኔን ጉዳይ ፀረ ሙስና ኮሚሽን አላጠናውም የምለው መነሻው ይኼ ስለሆነ ነው፡፡ ይኼ የሕግ ጥሰት ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ በእጃቸው ስለሆነ አዘመሩበት፡፡ መዘመር ብቻ ሳይሆን ፕሮግራምም ሠሩበት፡፡ ሕገ መንግሥቱን እናውቃለን የሚል ባለሥልጣን፣ አንድ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ሳይረጋገጥ በመገናኛ ብዙኃን ፕሮግራም መሥራትና ስለሱ መዘመር ምን ያህል ሕገወጥ ወንጀል መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ይኼንንም ያደረጉት የመገናኛ ብዙኃን ኮሚቴ ስብሳቢዎች በመሆናቸውና እንደፈለጉ ማድረግ ስለሚችሉ መሆኑንም አውቃለሁ፡፡ ቂምና በቀላቸውን ለመወጣት ሲፈልጉ ‹‹ወቅታዊ አጀንዳ›› በማለት የማጥቂያ ተኩስ መክፈት የለመዱትና የተካኑበት ሴራ መሆኑን ሁሉም ያውቃል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑም በኃላፊ ስሜት ስለሚመሩ ብዙ መገናኛ ብዙኃን ከመስመር ሊወጡ ችለዋል፡፡ ግለሰቦቹ ብዙ ተቋማትን ቢመሩም የለወጡት አንድ ተቋም እንኳን አይገኝም፡፡ ሰሞኑን ሚዲያው እውነትን ለሕዝብ እያቀረበ ነው፡፡ ይኼ የሚያረጋግጠው በአንድ አምባገነን ግለሰብ ይመራ የነበረው የሚዲያ ኮሚቴ ፈርሷል ማለት ነው፡፡ በክፋትና በተንኮል አገርን ለመምራት የሚፈልጉ የማፊያ ቡድን አባላት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ ይኼንንም በእኔ ላይና ከእኔ ጋር በታሰሩ ግለሰቦች ላይ ፈጽመውት ታይቷል፡፡ ሌላው ማንሳት የምፈልገው የጊዜ ቀጠሮን በሚመለከት ነው፡፡ ከሚገባው በላይ ለሦስት ወራት ክስ ሳይመሠረት የምርመራ ጊዜ እየተባለ የቀጠሮ ጊዜ ሲሰጥብን ቆይቷል፡፡ ክስ ተመሥርቶ የተሰጠን በስድስተኛ ወራችን በጥቅምት ወር 2006 .. ነው፡፡ ታስረን ነው ወንጀል የተፈለገልን፡፡ ክስ ከተመሠረተብን አራት ዓመታት በኋላም ወንጀል ያስፈልጉብን ነበር፡፡ በማፊያ ቡድናቸው መላኩ ያላግባብ አበል ወስዶ ከሆነ ፈልጉ ተብሎ ለብአዴን ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ነገር ግን እኔን ለማሳሰር የበቁ በመንግሥት ውስጥ የነበሩ የማፊያ ቡድን አባላት ወዲያና ወዲህ የሚንቀሳቀሱት በመንግሥት አበል መሆኑን ረስተውታል፡፡ በእኛ ላይ ግን ዳር የሚደርስ ነገር ሲጠፋ ታስረንም ወንጀል ይፈልጉብን ነበር፡፡                                                                              

ሪፖርተር፡-  በእናንተ ላይ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን አሰምቶ ፍርድ ቤቱም በሰጠው ብይን ይኼንኑ አረጋግጦ እንድትከላከሉ ብሏል፡፡ ክሱ ሐሰትና በማስረጃ ያልተደገፈ ነው ካሉ እንዴት ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹ እንደ ክሱ መስከረዋል ሊል ቻለ?

አቶ መላኩ፡-  ምስክሮች እየተደበደቡና ንብረታቸውን በመያዣ በመውሰድ እንዲመሰክሩ ተደርገዋል፡፡ አንዳንድ ምስክሮች ከመጀመርያው ምስክር እንደሚሆኑ በመናገራቸው ተለቀው መስክረዋል፡፡ ይኼም የሆነው ድብደባውንና እስራቱን በመፍራት ነው፡፡ አንመሰክርም ያሉ ባለሀብቶች እስከ መጨረሻው ከእኔ ጋር ታስረው ቆይተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በታሰሩበት ወቅት የአዲስ አበባ ምክር ቤት ተመራጭ ነበሩ፡፡ ያለመከሰስ መብት ያለዎት መሆኑ እየታወቀ የታሰሩ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤትም ይኼንን ሕግ አላስከበረም፡፡ አሠራሩ ይፈቅዳል? ወይስ ሌላ ምክንያት አለ?

አቶ መላኩ፡- እውነት ነው የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ነኝ፡፡ ያለመከሰስ መብት ቢኖረኝም መብት ሳይነሳ ታስሬያለሁ፡፡ ነገር ግን ያለመከሰስ መብቴ ሳይነሳ ልታሰር አይገባም፡፡ ግን እነዚያ ጥቂት አምባነኖች እንድታሰር ያደረጉት መብቴ እንኳን ሳይነሳ ነው፡፡ ከታሰርኩ በኋላ ጉዳዩ ተነስቶ ነበር፡፡ ግን ጨዋታ ነው፡፡ አስነስተው ወዲያው እንደሚያስሩህ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ሕግን ለመዳኘት የተሰየመ ዳኛ ያለመከሰስ መብት ያለው የምክር ቤት አባል እንደታሰረ እያወቀ፣ ለሕጉ ሲባል እንኳን ‹‹ሳይነሳ አላስርም›› አላለም፡፡ ዓቃቤ ሕጉም ሆኑ ዳኞች ለሕግ ክብር ሲሉ ማድረግ ነበረባቸው፡፡ የማናለብኝነቱ ጥግ የት እንደደረሰ የሚያሳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የእርስዎ ሹመት ‹‹በሚኒስትር ማዕረግ›› የሚል ነው፡፡ በሚኒስትር ማዕረግ ያሉ ተሿሚዎች በወንጀል ሲጠረጠሩ ጉዳያቸው የሚታየው በጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑን የሚደነግግ ሕግ አለ፡፡ የእርሰዎ ክስ በከፍተኛው ፍርድ ቤት መታየት በመጀመሩ ጥያቄ አስነስቶ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም ትርጉም እንዲሰጥበት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ልኮት ነበር፡፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የተከሳሾችን የመከራከር መብት ስለሚያከብርና ከሕግ መንግሥቱ አንቀጽ 25 አኳያ የአቶ መላኩ ክስ በከፍተኛው ፍርድ ቤት መታየት አለበት የሚል ትርጉም ሰጥቷል፡፡ እርስዎ ይኼንን ሒደት እንዴት ያዩታል?

አቶ መላኩ፡- በሚኒስትር ማዕረግ ያለ ሹም ጉዳዩ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይታያል የሚል ሕግ ቢኖርም እንዲታይ አላደረጉትም፡፡ ክሱ ዋጋ እንደሌለው ስለሚያውቁ፣ የክስ ሒደቱን በማራዘም እኔን ለመጉዳት ስትራቴጂ ተቀምጧል፡፡ ‹‹እዚያው ገብተህ ትበሰብሳታለህ›› ይሉኝ ነበር፡፡ ጉዳዩ ቶሎ እንዲያልቅ አይፈልጉም ነበር፡፡ ሁሉም ትክክል እንዳልሆነ ቢያውቁም ሕግ መጣስ የተለመደ በመሆኑ፣ አንዴ ወዲያ አንዴ ወዲህ እያሉ ማጓተቱን መርጠዋል፡፡ በወቅቱ ትርጉም ይሰጥባቸው የነበሩ ሕጎች እውነት ለዜጎች በሚጠቅም ሁኔታ ነው? ወይስ በወቅቱ የሥልጣኑን ማማ ለተቆናጠጠው አካል በሚጠቅም ሁኔታ ነው? የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ የእኔን ክስ በሚመለከት እኔን ለመጥቀም ሳይሆን፣ ከእኔ ክስና መታሰር ጀርባ ያሉ የማፊያ ቡድን አባላት ለማስደሰት የተደረገ ነው፡፡ የእኔን ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ በቅርቡ የወጣው የጉምሩክ ሕግም ‹‹ለተከሳሹ እስከጠቀመው ድረስ ተፈጻሚ ይሆናል›› የሚለውን ፍርድ ቤቱ ተጠቅሞ ባለሀብቶችን ነፃ ሲያደርግ፣ ‹‹የመንግሥት ሠራተኛን አይመለከትም ተብዬ ተከላከል›› ተብያለሁ፡፡ ይኼ ሒደት የሚያሳየው ‹‹ልትቀጣው ያሰብከው ሰውዬና እንድትቀጣለት የሚፈልገው ሰውዬ ፍላጎት ምንድነው?›› እየተባለ ታስቦ ነው ሕግ እየተተረጎመ ያለው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሕግን ሲያስቀምጥ ለባለሀብትና ለመንግሥት ሠራተኛ ብሎ አላስቀመጠም፡፡ ከላይ እስከ ታች በተደራጀ ሁኔታ የማጥቃት ዘመቻ ስለነበር አተረጓጎሙም ያንን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ በአብዛኛው የእኛ ተቃውሞ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ ፍርድ ቤቱ ጠበቆቼን ያስፈራራ ነበር፡፡ የፍርድ ቤቱን አካሄድ የተቃወመው ጠበቃዬ አቶ ተሻገር ደሳለኝ እስከ መከሰስ ደርሷል፡፡ ችሎቱን ከሚመሩትም ዳኞች መካከል፣ የክርክሩን ሒደት በአግባቡ የመሩና ከችሎት መነሳት እስከ መባረር የደረሱትን ዳኛ ግዛቸው ምትኩ ማስታወስ ይቻላል፡፡ የሕግ ትርጉሙ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የችሎት አመራር ሒደቱም ላይ ግልጽ በደል ሲፈጸም ነበር፡፡ የዓቃቤ ሕግ ማንኛውም ጥያቄና ማሳሰቢያ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ በዳኛም ጭምር ይታገዝ ነበር፡፡ ሒደቱ ሕግን ያዛባና ፍትሕን ያጎደለ ነበር፡፡

በእኛ ላይ የደረሰው በደል ብዙ ነው፡፡ ታስሬ እንኳን ሊጠይቁኝ የመጡ ሰዎች ወዲያውኑ ማስፈራራት ይደርስባቸው ነበር፡፡ በዙሪያዬ ያለ ሰው ሁሉ በደኅንነት እንዲጠናና እንዲመረመር ተደርጓል፡፡ ይኼ ሁሉ የሚደረገው ግን በሕዝብ ገንዘብ ነው፡፡ ለጥሩ ነገር ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ ግን ሰውን ለማጥቃት መሆኑ ነው የሚያሳዝነው፡፡ የመከላከያ ምስክሮቻችንን ያስፈራሯቸው ስለነበር ለመመስከር እንደሚፈሩ ነግረውን የቀሩ አሉ፡፡ አንድ ምስክር ከአሳሳሪዎቼ አንዱን ፈቃድ ጠይቆ እንደ መጣ ነግሮኛል፡፡ ይኼ ቡድን አገር ለማጥፋት በመንግሥት ውስጥ ሆኖ የተደራጀ የማፊያ ቡድን ነበር፡፡ የእነሱ ድርጊት ሄዶ ሄዶ አገር ማፍረስ የሚችል ማዕበል እስከ ማስነሳት ደርሶ ሕዝቡም ሆነ አንዳንድ የድርጅቶቹ አባላት በማለቃቸው፣ የመንግሥት ደቀ መዝሙር ሆነው ሕዝብ ፊት በመቅረብ በተግባር ግን ሕገ መንግሥቱን የሚንዱ መሆናቸው ታውቆባቸዋል፡፡ እነዚህ ጥቂት የማፊያ ቡድን አባላት እኔን ለማጥፋትና ለመግደል ሕጋዊ አስመስለው የሄዱበት ርቀት ብዙ ባለሙያዎችን ለጉዳት ዳርጓል፡፡ ብዙ ባለሙያዎችም ተቋሙን እንዲለቁ ተደርገዋል፡፡ አንድን ግለሰብ ማጥፋት ሲቀል ሕግን ሽፋን በማድረግ ተቋም ማፍረስ ከሁሉም የከፋ ወንጀል ነው፡፡ ሲፈጸም የነበረው ይኼ በመሆኑ ሒደቱ ኢሕገ መንግሥታዊ መሆኑን ያሳያል፡፡ እነዚህ ቁጥራቸው ከስድስት የማይበልጡ ሰዎች ካለቸው የዕውቀት ደረጃ አንፃር በመድረክ ላይ በምትሰጠው አስተያየትና ሒስ ይፈርጁሃል፡፡ በሐሳብ ስትለይ ታፔላ ይለጥፉልሃል፡፡ ‹‹ቅንጅት ነው›› ብለው አጥንተውኛል፡፡

ስለወርቅ ማዕድን ኦፕሬሽን ስንሠራ በአጋጣሚ ወደ ሥራው የገቡት የትግራይ ተወላጆች ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ትግራዮችን ለማጥቃት ነው›› ብሎ ደኅንነቱ አጥንቶ ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሪፖርት አቀረበ፡፡ ነገር ግን አንድም ኦፕሬሽን ለእሳቸው ሳላሳውቅ ስለማልሠራ ወደሳቸው ያቀረቡት ሪፖርት እንደፈለጉት አልሆነላቸውም፡፡ እኔ የታክስ ክፍተቶችን አጠናና ምን ልሠራ እንዳሰብኩ ከእሳቸው ጋር እወያያለሁ፡፡ ‹‹ቀጥል›› ሲሉኝ እቀጥላለሁ፡፡ እሳቸው ያላወቁትን አልሠራም፡፡ እኔ ማንንም ከማንም አብልጬ ወይም ማንንም ለመጉዳት የምሠራበት ምክንያት አልነበረኝም፡፡ ለእኔ ሁሉም ዜጋ እኩል ነው፡፡ የአዲስ አበባ ገቢን በሚመለከት ከቁርጥ ሥራ ወደ ታክስ ሲስተም ለማስገባት በውክልና ወስደን ስንሠራ፣ ‹‹መንግሥትና ሕዝብ ሊያጋጭ ነው›› በማለት ደኅንነቱ አጥንቶ ለአቶ መለስ አቅርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን እሳቸው የሚያውቁት ሥራ በመሆኑ ምንም አላሉም፡፡ አገርንም የተወለድኩበትንም ክልል እንደ ዜጋ ከመርዳት አንፃር አልማ ውስጥ በኮሚቴ ተሳትፌ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተን ነበር፡፡ ገቢ ከማሰባሰብ ባለፈ የክልሉ ተወላጆች ወደ አክሲዮን እንዲያድግ ሐሳብ አምጥተን ዓባይ ባንክን ጀምረን ነበር፡፡ የጎንደር የጥምቀት በዓል ደግሞ ለከተማው ትልቅ የገቢ ምንጭ ይሆናል በሚል ፕሮጀክት ቀርፀን የአፄ ቴዎድሮስን ሐውልት የማቆምና ሌሎች ሥራዎችን እንሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን የማፊያ ቡድኑ ውስጥ ለውስጥ ጥናት እንዳደረገ በመግለጽ ‹‹የትምክህት ኃይል እንዲሰማራ አደረገ›› ነው ያሉት፡፡ እነሱ ያሉትን ካልሠራህ ጣልቃ ሲገቡ ‹‹ልክ ናችሁ›› ካላልክ በአንተ ላይ የሚጀመው ሴራ ቁጥር ሥፍር የለውም፡፡

ሕገ መንግሥቱ ግልጽ ነው፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት ክልልና አካባቢ ተዘዋውሮ መኖርና መሥራት እንደሚችል ይገልጻል፡፡ ይኼንንም በማስመልከት በአንዳንድ ክልሎች ጥሩ ያልሆነ እንቅስቃሴ ይታይ ስለነበር፣ ያንንም ከሥሩ ለመፍታት እንቅስቃሴ ጀምሬ ነበር፡፡ አሁን ይኼው ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ተገብቷል፡፡ እነዚህ ቡድኖች ስለሕገ መንግሥቱ በመድረክ ላይ ሲናገሩ ደቀ መዝሙር ናቸው፡፡ መሬት ላይ ግን ምንም የለም፡፡ ተግባራዊ እየተደረገ አልነበረም፡፡ እነዚህ በመንግሥት ውስጥ ተደራጅተው የነበሩ ጥቂት የማፊያ ቡድን አባላት በታክስ ችግር አንድ ባለሀብት ስናስር ‹‹ለምን?›› ብለው ይንጫጫሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ሚስተር ኤክስን እሰር›› ብለው ደግሞ ጥያቄ ያቀርቡልኛል፡፡ በእኔ እምነት ቦታው ላይ የተቀመጥኩት የታክስ ሕጉን ለማስከበር ነው፡፡ የሌሎችን ፍላጎት ለማስከበር አይደለም፡፡ ይኼ ትልቁ ጣልቃ ገብነት ነበር፡፡ በተለይ አቶ መለስ ካረፉ በኋላ ጥያቄያቸውና ጣልቃ ገብነታቸው እየበዛ መጣ፡፡ በታክስ ማጭበርበር የታሰሩና እኛ እንድንፈታላቸው ሲጠይቁን ‹‹አይቻልም›› ያልናቸውን፣ በተለይ ከቡድኑ መካከል ከፍተኛ ጨዋታ ይጫወቱ የነበሩት ባለሥልጣን፣ ጠዋት ዋስትና የተከለከለ ነጋዴ ከሰዓት በእሳቸው ትዕዛዝ በዋስ ይወጣል፡፡ በርካታ ዓመታት ሊፈረድበት የሚችልን ወንጀለኛ እሳቸው በፍርድ ቤት ላይ በሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት በገደብ እንዲወጣ ያደርጉታል፡፡ ይኼንን ማድረግ ‹‹አይቻልም›› ባልክ ቁጥር ከፍ እያለ መጥቶ ለእስር ተዳርገናል፡፡  

ሪፖርተር፡- በአቶ በረከት ስምኦን ባለቤት ስም ከውጭ አገር የገባ የፊልም ካሜራ እንዲወረስ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ ይኼ የሆነው ደግሞ ከአቶ በረከት ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ግጭት ስለነበራችሁ ነው ይባላል፡፡ እስኪ ስለዚህ ነገር ያስረዱን?

አቶ መላኩ፡- ልክ ነው፡፡ በአቶ በረከት ባለቤት ስም ዘመናዊ የፊልም ካሜራ ገብቶ ተይዟል፡፡ የጉምሩክ ሠራተኞች ‹‹የአቶ በረከት ባለቤት ዕቃ ነው›› ሲሉኝ፣ ‹‹ይሁና እንደ ማንኛውም ዜጋ መስተናገድ አለባቸው›› ብያለሁ፡፡ ታክስና ቀረጡን መክፈል ከቻሉ ማውጣት ይችላሉ፡፡ ካልከፈሉ ግን ዕቃው መወረስ አለበት ብዬ ዕቃው ተወርሷል፡፡ ይኼንን ያደረግኩት ከአቶ በረከት ጋር ግጭት ወይም ጥላቻ ስላለኝ አይደለም፡፡ በቦታው የተቀመጥኩት ሕግ ለማስከበር በመሆኑ ነው፡፡ እሳቸው ግን በእኔ ለይ ጥላቻ እያደረባቸው የመጣ ይመስለኛል፡፡ ይኼንንም በሚመለከት በብአዴን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ፊት አንስቼ ግምገማ ተካሂዶበታል፡፡ መጽሐፋቸውን ውጭ አገር አሳትመው ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ወደ ውጭ ለመሸጥ ሲፈልጉ ‹‹አሠራሩን ተከተሉ›› ነው ያልኳቸው፡፡ ግን ያንን አላደረጉም፡፡ በተለያየ መንገድ እንዲወጣና እንዲሸጥ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ምን ያደርጋል የግምገማው መድረክ እኔን ማጥቂያና ቂም መወጫ አድርጎኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ጣልቃ ገብነቱ እየባሰና ሕገወጥ ሥራዎች እየበረከቱ የመጡት ከአቶ መለስ ሞት በኋላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አላስረዷቸውም?

አቶ መላኩ፡- አስረድቻቸዋለሁ፡፡ እነ ማን በምን ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ እንደሆነ ስነግራቸው ‹‹እኔም አውቀዋለሁ›› ብለውኛል፡፡ ከቡድኑ አባላት ውስጥ አንዳንዶቹን እቀርባቸው ስለነበር የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ በምክር መልክም ነግሬያቸው ነበር፡፡ ለኢሕአዴግም ጥሩ አይደለም ብዬ በመምከሬ ተመልሰው ለእኔ ጠላት ሆኑኝ፡፡ ሦስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከአንድ ድርጅት ሆነው በእኔ ላይ ውሳኔ በማሳለፍ፣ ለብአዴን ደግሞ ሌላኛው የቡድኑ አባል አስተላለፈ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ሳስረዳቸው ‹‹አውቃለሁ፡፡ ጉሮሮአቸው ላይ ስለቆምክ ነው፡፡ ከጎንህ አለሁ ሥራህን ቀጥል…›› ብለውኝ ነበር፡፡ አሁን ይፋ የወጣውን በተለያየ የልማት ሴክተር ይደረግ የነበረውን ዝርፊያ አስቀድሜ ነገሬያቸው ነበር፡፡ በግልባጩ ወሬው እየወጣ ለእኔ መምቻ ነው የሆነው፡፡ ሌላ ላነሳልህ የምፈልገው ነገር ሁለት ባለሥልጣናት ሪፖርተር ጋዜጣን ጨምሮ እንዳስር አንድ ጥናት አጥንተው አምጥተውልኝ ነበር፡፡ ማስታወቂያ የሚሰጡትን ድርጅቶች (ስም ተጠቅሷል) ባለቤቶች እንዳስር ዝርዝር ሰጥተውኝ ነበር፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ በራሱ ኅትመት ለመጀመር ማተሚያ ማሽን እያስመጣ ስለሆነ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ አድርግም ተብዬ ነበር፡፡ ምላሼ ግን ማስታወቂያ የሚሰጡት ድርጅቶች የታክስ ማጭበርበር እስካልሠሩ ድረስ መብታቸው መሆኑን፣ ጋዜጣውም ማሽን ማስገባት መብቱ እንደሆነ ምላሽ ሰጥቻለሁ፡፡ እስከዚህ ድረስ የታክስ ሲስተሙና ሕጉ ለሌላ መሣሪያ እንዲሆን ማድረግ ይፈልጉ ነበር፡፡ ያንን አላደረግኩም፡፡ ሥራዬ ሕግን ማስከበር ስለነበር፡፡ በተመሳሳይ ኤፈርትና ጥረት ወደ ታክስ ሲስተም እንዲገቡና ብድራቸውንም እንዲከፍሉ ብዙ መንገድ ተጉዤ አቶ መለስም ያውቁት ስለነበር እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በዚህ ሒደት ላመሠግነው የምፈልገው አቶ ዮሴፍ ረታ የጥረት ድርጅቶች ወደ ታክስ ሲስተሙ እንዲገቡ ብዙ ጥረት አድርጓል፡፡ እነዚህ እነዚህ ሲደመሩ ‹‹ሌላ የፖለቲካ አመለካከት አለው›› ተብዬ ተፈረጅኩኝ፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቻው ሲናገሩ ‹‹ያልታደሱ የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች›› ያሏቸው አሉ፡፡ በእኔ እምነት ያልታደሱ ሳይሆን የማይታደሱም አሉ፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን እንደፈለጉ ያደረጉ ናቸው፡፡ አቶ መለስ ከደኅንነትና ከሌሎች ተቋማት ጋር እንድሠራ አድርገውኝ ጀምሬ ነበር፡፡ አካሄዳቸውን ሳያው፣ ይኼ ተቋም ቢወድቅ እንደምጠየቅና እንደምወቀስ ስለገባኝ ችግሩንና አሠራሩን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድቼ ወጥቻለሁ፡፡ ኢንሳ እንደፈለገ እንዲፈነጭ ይፈልጉ ከነበሩ አመራሮችም ጋር ተጋጭቼ ነበር፡፡ ኢንሳ ብዙ ፕሮጀክቶችን ይወስድና እንደፈለገ ሊያደርግ ይፈልግ ስለነበር ለእኔ ሊስማማኝ አልቻለም፡፡ መከላከያም ከኮንትሮባንድ ጋር በተያያዘ ያለበትን ሁኔታ ለአቶ መለስ ሪፖርት አቅርቤያለሁ፡፡ እነዚህ መሰል ነገሮች ተደምረው ታፔላ ይለጠፍልሃል፡፡ በእኔ እምነት ኢሕአዴግ ውስጥ ሆነህ ለውጥ ማምጣት ይቻል ነበር፡፡ ይኼንን ሁሉ የሚያደርገው መንግሥት ሳይሆን ጥቂት በመንግሥት ውስጥ ጡንቻቸው የጠነከረ ማፊያዎች ናቸው፡፡ የእነሱ ሥራ በእኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ተከሳሾች ላይ ነው፡፡ በብዙ ታሳሪዎች በተለይ በአማራና በኦሮሞ ተወላጆች ላይ በእነዚህ የማፊያ ቡድን አባላት ምክንያት የደረሰው በደል፣ ሰቆቃ፣ ግርፋትና ሞት መቼም መቼም የሚደገም አይመስለኝም፡፡ አካል በማጉደልና ዘርን እንዳይተኩ ማኮላሸት የሰው ልጅ ያደርገዋል በማይባልበት ሁኔታ ተፈጽሟል፡፡

አንድ ማረሚያ ቤት ካለ እስረኛ ጋር እጃችን ተያይዞ ታስረን ወደ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሄድን፡፡ በመንገድ ላይ እየሄድን ስናወራ በጣም ተጨናንቋል፡፡ ‹‹ምነው ምን ሆነሃል?›› ብዬ ስጠይቀው ተመርምራ ምናልባት አንዷ ፍሬ ልትሠራ ትችላለች ብሎኝ ውጤት ለመስማት ነው የምሄደው አለኝ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብልቱ ተመትቶ አንዱ የዘርፍሬ በመፍሰሱ ነው፡፡ ስንመለስ ስንገናኝ ‹‹መውለድ ትችላለህ ተባልኩ›› ብሎ የነበረው ደስታ ለእኔ አስደሳች ሳይሆን አስለቃሽ ነበር፡፡ ወጣቶች እንዳይወልዱ እየተኮላሹ ነው፡፡ ይኼ ዘር ማጥፋት ነው፡፡ በዘር ለይቶ መደብደብና ዘሩን እንዳይተካ ማድረግ፡፡ እነዚህን ነገሮች የማነሳው ለበቀል አይደለም፡፡ የችግሩ ስፋት ምን ያህል እንደደረሰ ለመጠቆም ነው፡፡ እኔ ከሥራ ጋር እንጂ በግሌ ከማንም ጋር አልገናኝም፡፡ ከቀድሞ የአቅም ግንባታ ሚኒስትር አቶ ተፈራ ዋልዋ ጋር ብቻ ነበር የምገናኘው፡፡ የነበረውን ችግር በቁንፅሏ የምናገረው እንደ መማሪያ እንዲያገለግል በሚል ነው፡፡ በተረፈ የደረሰብኝ በደል ሆነ ያደረሱብኝን ቡድኖችም ሆነ ግለሰቦች ይቅር ብያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በተከሰሱባቸው ክሶች ከአንድና ሁለቱ በስተቀር ሌሎቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 411 እና 407 በመተላለፍ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት የሚሉ ናቸው፡፡ እስኪ ስለክሶቹ ይንገሩን?

አቶ መላኩ፡- ክሶቹን በሚመለከት ሁለት ነገሮች ላንሳ፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት መታየት የነበረበትን በከፍተኛ ፍርድ ቤት በመመሥረት እንዲጓተት በማድረግ ተስፋ ማስቆረጥ ነው፡፡ ሌላው አንድና ሁለት መሆን የሚችሉትን በአንድ መዝገብ እስከ 93 ክሶች በማቅረብ ማንዛዛት ነበር፡፡ እኔ በግሌ 12 ክሶች ቀርበውብኛል፡፡ ሲጠቃለሉ ግን አንድ ክስ ናቸው፡፡ በአንድ መብት፣ በአንድ ድንጋጌና በአንድ ድርጊት ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ የወንጀል ሕጉ አንድቀጽ 61 ይኼንን ይጠቅሳል፡፡ ሁለተኛው ነገር በሕጉ መሠረት ክሶቹ ሊያስከስሱኝ የሚችሉ አይደሉም፡፡ የወንጀል ሕግ 411 ሦስት ነገሮችን ያነሳል፡፡ ጥቅም ለማስገኘት፣ ጥቅም ለማግኘትና የሚጎዳ ተግባርን መፈጸምን አካቶ መያዝ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ለማስመሰል ባለሀብቶችን አብረው ለጠፏቸው፡፡ እኔ ምንም ጥቅም አላገኘሁም፣ አላስገኘሁም ወይም በማንም ላይ ጉዳት አልደረሰም፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ስለመፈጸማቸው አንድም የቀረበ ማስረጃ የለም፡፡ እንዲያውም ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሁሉም ባለሀብቶች በአግባቡ ታክስና ቀረጥ ስለመክፈላቸው ነው ማስረጃ የላከው፡፡ ክስ አድርገው ያቀረቡብን ለሪፎርም ሥራው ያዘጋጀናቸውን መመርያና ፎርሞች ሰብስበው ነው፡፡ በአጠቃላይ ወንጀሉን ማቋቋም የሚችሉ ነገሮች በሌሉበት ነው ክስ የመሠረቱብኝ፡፡ በማናቸውም ባለሀብቶች ላይ አልተመሰከረባቸውም፡፡ ወደ ክሱ ስመለስ የተወሰኑትን ልጠቁም፡፡ ባለሀብቶቹ የተከሰሱት አራጣ ማበደርና ታክስ ማጭበርበር በሚል ነው፡፡ አራጣ የገቢዎችና ጉምሩክ ሥልጣንን አይመለከትም፡፡ ታክስ ያጭበረበሩትን ስናጠና የተገኘው የታክስ ውሳኔ በጣም ከፍተኛ የግብር መጠን አሳየ፡፡ ይኼንን ከአቶ መለስ ጋር ስንወያይ ‹‹የገቢ ምንጩን አጣራው፡፡ ከታክስ ትርፍ አንፃር በጣም የተጋነን በመሆኑ ምናልባት የሽብርና የሙስናና ገንዘብ እንዳይሆን›› አሉ፡፡ ምንጩ ሲጣራ አራጣ ሆኖ ተገኘ፡፡ እኛ ልንከስ የነበረው ታክስ በማጭበርበር ስለነበር ከፍትሕ ሚኒስቴር ውክልና ወስደን አራጣን ተደራቢ ክስ አደረግነው፡፡

በዚህ ጊዜ አቶ ከተማ ከበደ የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት የተገኘባቸው ወንጀል የለም፡፡ እንዲያውም ከፍተኛ ግብር ከፋይ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ ክሱን ሲመሠርት ‹‹ፍትሕ ሚኒስቴር አጥንቶ ክስ እንዲመሠረትባቸው ለገቢዎችና ጉምሩክ ውክልና ሲሰጥ አቶ ከተማ ከበደ የተካተቱ ቢሆንም እንዳይከሰሱ አድርጓል›› የሚል ነው፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር በመከላከያነት ቀርቦ ግን ‹‹እኔ ያስጠናሁት ነገር የለም›› ብሏል፡፡ አቶ ከተማን በሚመለከት አንድ የብድር ውል መጥቶልኝ አራጣን የሚያመለክት ባለመሆኑ መልሼው ነበር፡፡ ነገር ግን አቶ ሳሙኤል ታደሰ የሚባል የእኛ ዓቃቤ ሕግ አቶ ከተማ እንዳይከሰሱ የተደረገው አቶ ገብረዋህድ ተደራድሮበት ነው ብሎኛል ብለው ሲያነጋግሩኝ፣ አለመሆኑንና ማበደር ደግሞ አለመከልከሉን ነግሬያቸው ነበር፡፡ ቀጥሎ የሚሠሩትን ተንኮል አውቅ ስለበርም አቶ መለስን ሳነጋግራቸው ‹‹ጉዳዩን ለደኅንነት አሳልፍና ስጥ፣ እነሱ ይከታተሉት›› ብለውኝ ስለነበር ወዲያውኑ ሰጥቻለሁ፡፡ ያንን የመንደር ወሬ በመለቃቀምና አቶ ከበደ ቅንጅት አሸንፏል በማለት አሜሪካ ሲጋብዝህ ነበር በማለት ተሰብሰቦ ክስ ሆኖ ቀረበብኝ፡፡ ሌሎቹም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ከቀረጥ ነፃ ያስገቡዋቸውን ቁሳቁሶችን በአግባቡ ሥራ ላይ አውለዋል ወይስ አላዋሉም የሚለውን አጥንተን፣ ችግር የተገኘባቸው በርካታ ሆቴሎች በመሆናቸው በአስተዳደር በኩል እንዲቀጡ አደረግሁ፡፡ ይህም በአዋጅ የተሰጠኝ ሥልጣን ነው፡፡ ብዙ ሆቴሎች ቢሆኑም የኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ብቻ ተመዞ ወደ ክስ መጣና ‹‹በአስተዳደራዊ ጉዳይ ፍቱለት›› ተባለ፡፡ በኋላም የመጣው የጉምሩክ ሕግ በአስተዳዳር በኩል ይፈታል በማለቱ ነጋዴዎቹ ነፃ ሲባሉ፣ እኛን ተከላከሉ አሉን፡፡ 2005 .. በርካታ የጨረታ ንግዶችና ክምችቶችን አጥንተን ነበር፡፡ ‹‹ኤርታሌ ገባህ፣ አርፈህ ብትቀመጥ ይሻላል›› የሚል ማስጠንቀቂያ ደርሶኝ ነበር፡፡ እኔ ግን ሥራዬን እየሠራሁ በእጄ ላይ የብረትና የዶላር ምንዛሪ ጥናቶች ነበሩኝ፡፡ ሳልተገብራቸው ታሰርኩኝ፡፡ ጥናቶቹን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (/) ቢወስዷቸው ይጠቀማሉ፡፡ ሌላው ክስ የዶ/ ፍቅሩ ማሩ ነው፡፡ ክስ አቋርጠሃል ነው የተባልኩት፡፡ ክስ ማቋረጥ በአዋጅ የተሰጠኝ ሥልጣን ነው፡፡ ነገር ግን እሳቸው የተከሰሱበት ጉዳይ 85 ሺሕ ብር ታክስ የሚያስከፍል የሕክምና መሣሪያ ነው፡፡ ቢሆንም በአስተዳደር በኩል የሚያልቅ ነበር፡፡ ዶክተሩ ተከሰው ነበር፡፡ ነገር ግን ይኼንን ነገር በአስተዳዳር በኩል ብትፈቱት ብለው የፀረ ሙስና ኮሚሽነሩ አቶ ዓሊ ሱሌማንና / ቴዎድሮስ አድሃኖም እኚህ ሰው ለአገር ከሚሰጡት ጥቅም አንፃር ብታዩት የሚል ሐሳብ ሲያቀርቡልኝ፣ ዕቃውን ወርሰን በአስተዳደር ፈታነው፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት በአቶ በረከት ባለቤት ስም የገባውንና በሚሊዮኖች የሚቆጠር የታክስ ገቢ የሚያስገኘውን የፊልም ካሜራንም ወርሰን በአስተዳደር በኩል ነው የፈታነው፡፡ መክሰስ ነበረብህ ከተባለ የእሳቸውንም ጉዳይ ማንሳትና የክሱ አካል ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ዓላማቸው ሌላ ስለነበር ግን የተፈለገው ዶክተሩን መክሰስ ነበር፣ አደረጉት፡፡ ለእኛ ክስ ሌላ ምክንያት ያደረጉት ተመሳሳይ ሕገወጥ መመርያ አውጥተሃል የሚል ነው፡፡ ጉራማይሌ የነበረውን የታክስ አሰባሰብ ሥርዓት ወጥ ለማድረግ የተዘጋጀ መመርያ የነበረና አሁንም እየሠሩበት ነው፡፡ በአጠቃላይ እኛ ላይ ከባድ ሙስና ብለው የዘመሩት ለእኔ የሚያሳየኝ፣ እዚህች አገር ውስጥ ሙስና የለም ማለት ነው ወይም ሙሰኞቹ ሙሰኛ ያልሆኑትን እያጠቁ የፖለቲካ አጀንዳውን እያሰቃዩ ከተጠያቂኒት እየዳኑበት መሆኑን ነው፡፡ እንደኔ እምነት ግን ሙሰኞች የአጀንዳ ማስቀየሪያ አድርገውታል፡፡ ቂማቸውን ለመወጣት ጥረት አድርገዋል፡፡ እኔ በበኩሌ አገሬን አልበደልኩም፣ አልሰረቅኩም፣ አቅሜ የፈቀደውን ለመሥራት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የክሶቹን ዓይነትና በውስጣቸው ያለውን ቁም ነገር አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ለተሻለ ፍትሕ አሰጣጥ እንዲረዳ በማለት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የሰነድ ማስረጃዎችንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ምስክሮችን በመስማት ሲያከራክር አምስት ዓመታትን ወስዷል፡፡ ጊዜውንና የክሶቹን ሁኔታ እንዴት ይመዝኑታል?

አቶ መላኩ፡- እኔ ከመሰልቸቴ ብዛት በችሎት ላይም እዚያው ማረሚያ ቤት እያለሁ ፍርዳችሁን ላኩልኝ ብያለሁ፡፡ ለሥርዓት ማሟያ መመላለስ ካልሆነ በስተቀር ምንም ፋይዳ አልነበረውም፡፡ አንደኛ አካሄዱን ጥሷል፡፡ ፍርዱን ለማፋጠን ቢፈልግ ኖሮ በታትኖ ከማቅረብ ይልቅ፣ በአንድና በሁለት ክስ ማጠቃቀልና ማቅረብ ይቻል ነበር፡፡ ሆን ተብሎ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ አንዳንዶችኧረ ክሱ ተንዛዛ ወይ ይቋረጥ›› ብለው ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ሲያማክሩ ‹‹መንግሥት ይዋረዳል እንደምንም ብላችሁ ጨርሱ›› መባላቸውን ከተፈታሁ በኋላ አጫውተውኛል፡፡ እውነታው ይኼው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አቶ ከተማ ከበደና እርስዎ የጥቅም ትስስር እንዳላችሁ ክሱ ይገልጻል፡፡ እናንተ ደግሞ ትውውቃችሁ በእስር ቤት መሆኑን ለፍርድ ቤት ጭምር አስረድታችኋል፡፡ እውነታው ምንድነው?

አቶ መላኩ፡-  ከእሳቸው ጋር ብቻ አይደለም፡፡ ከኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ባለቤት ጋር፣ ከዶ/ ፍቅሩ ማሩና ከሌሎች በተለጣፊነት ከተከሰሱት ነጋዴዎች ጋር ሥውር ግንኙነት አለው ተብያለሁ፡፡ አቶ ከተማን ያገኘኋቸው ለተወሰኑ ደቂቃዎች በአልማ ጉባዔ ላይ ነው፡፡ ይኼም ለአልማ ቃል ገብተው ስለነበር እዚያ በመገኘታቸው ነው፡፡ ከዚያ በፊት አያውቁኝም፣ እኔም አላውቃቸውም፡፡ የሚገርመው ግን ማዕከላዊ ታስረን እያለ በምርምራ ላይ ‹‹ከተማ ከበደን ያልከሰሰው ለአልማ ገንዘብ ስለረዳ ነው›› ብለው ጠይቀውኛል፡፡ ይኼ ‹‹የትምክህት ኃይል እንዲያንሠራራ አደረገ›› ከሚለው አስተሳሰብ የመነጨና አማሮችን ለይቶ የመጠየቅ ጉዳይ ሆኖ ነው ለእኔ የገባኝ፡፡ ብዙዎቹን ያወቅኳቸው ማረሚያ ቤት ነው፡፡ እስር ቤት አይደለም፡፡ ከእነሱም ጋር፣ ከሌሎቹም ጋር ተዋውቄያለሁ፡፡ እነ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌንም እዚያው ነው ያገኘኋቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የመጨረሻ የቅጣት ውሳኔ ሊነገራችሁ ቀጠሮ የያዛችሁበት ቀን ከመድረሱ ሦስት ቀናት በፊት፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክሳችሁን አቋርጦ ከእስር እንድትፈቱ ተደርጓል፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

አቶ መላኩ፡- እኔ በአምስት ክሶች ቀደም ባለ ብይን ነፃ ተብያለሁ፡፡ በሦስት ክሶች ጥፋተኛ ተብዬ ነበር፡፡ አራት ክሶች ደግሞ ውሳኔ አላገኙም ነበር፡፡ ተቀጥሬባቸው የነበሩትን ክሶች በሚገባ በመከላከሌ ነፃ እባላለሁ የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ዞሮ ዞሮ መንግሥት ይቋረጥ በማለቱ ከእኔ ውጪ የሆነ ነውና ተቀብያለሁ፡፡ በእኔ እምነትና ምርጫዬ የነበረው ውሳኔው ተነግሮኝ ብፈታ የተሻለ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከታሰርኩት በላይ በእስር ሊያስቆየኝ የሚችል ቅጣት ይጣልብኛል ብዬ ስለማላምን ነው፡፡ በእርግጥ ከእስር መውጣት ለቤተሰብና ለወገን የሚሰጠው እረፍት አለ፡፡ ከእዚያ አንፃር ተቀብያለሁ፡፡ እኔ ለአገሬ ሠርቻለሁ እንጂ በድያለሁ ብዬ ስለማላምን የመጣውን ለመቀበል ከመጀመርያው ጀምሮ ዝግጁ ነበርኩ፡፡

ሪፖርተር፡-  የማፊያ ቡድን አባላት ያሉዋቸው ግለሰቦችን ማንነት ይንገሩን እስቲ?

አቶ መላኩ፡- የእነሱን ማንነት አሁን መግለጹ ከደኅንነት አንፃር ጥሩ አይሆንም፡፡ ድርጊታቸው ግን ማንነታቸውን ስለሚናገር እዚህ ላይ ብንተወው ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  ከአምስት ዓመታት የእስር ቆይታ በኋላ ከእስር ተፈትተው ከቤተሰብ ጋር ተቀላቅለዋል፡፡ አሁን ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ እርስዎ ወደ እስር ቤት ሲገቡ ከነበረበት ሁኔታ ተቀይሮ ከፍተኛ እመርታ እያሳየ ነው፡፡ ሁለቱን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ወቅቶች እንዴት ያነፃፅሯቸዋል? ምንስ ይመክራሉ?

አቶ መላኩ፡- አሁን እየታየ ያለው ለውጥ ትልቅ ነው ብዬ የምወስደው፡፡ ይህ ለውጥ በመጀመርያ በእግዚአብሔር፣ በመቀጠል በሕዝብ ብሶት የመጣ ነው፡፡ ይኼ ለአገር ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ በእኔ እምነት ከእግዚአብሔርና ከሕዝቡ የመጣ ለውጥ በምንም መለኪያ ወደ ኋላ እንዳይመለስ መሥራት ይጠይቃል፡፡ ብዙ የለውጥ ዕድሎችን አልፈን ሊሆን ይችላል፡፡ ይኼ የለውጥ ዕድል ግን ማለፍ የለበትም፡፡ ትልቅና ታሪካዊ መንታ መንገድ ላይ ነን ብዬ ነው የማስበው፡፡ አጋጣሚ ዕድልና ሥጋት አለው፡፡ በመሆኑም ዕድሉን የመጠቀምና ሥጋቱን የመቀነስ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በጥንቃቄና በሥርዓት ሊመራ የሚገባውና አገራችን ልታጣው የማይገባ ዕድል ነው፡፡ ስለዚህ አጋጣሚውንና ሥጋቱን ለመጠቀምና ለመቀነስ፣ በአጭር ጊዜና በረዥም ጊዜ የሚሠሩ ሥራዎችን ለይቶ ማስቀመጥ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በመንግሥትና በመሪው ፓርቲ መሠራት አለበት ብዬ የማምነው አንደኛ ይኼንን የለውጥ ማዕበል ማስፋፋትና መሬት ማስረገጥ ያስፈልጋል፡፡ መሬት የሚረግጠው ደግሞ ሕዝቡ ውስጥ ምን እንሠራለን? በተቋማት ውስጥ ምን እንሠራለን? በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥስ ምንድነው ሊሠራ የሚገባው የሚለውን አስተሳሰብ የማስረፅ አንዱና ትልቁ ሥራ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ምሰሶዎች ተብለው የሚጠቀሱት የሰላም፣ የዴሞክራሲ፣ የፍትሕና የአካባቢ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነዚህ የማይነጣጠሉና አብረው ሊተገበሩ የሚገቡ መርህ ናቸው፡፡ እስረኞች የታሰሩበትን ሁኔታ እያጣሩና እየለዩ መፍታት ተገቢ ነው፣ ተጀምሯል፡፡ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት በመንግሥትና በድርጅቶች መካከል መድረኮች በማዘጋጀት፣ ሕዝቡን ያሳተፈ በወቅታዊ ሁኔታዎችና በልማት ዙሪያ ውይይት ማካሄድና ‹‹ምን ይደረግ›› ለሚለው ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ መፍተሔ ማፈላለግ ተገቢና ወሳኝ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን ከዜሮ መጀመር ተገቢ ነው እላለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) አመራሮችን እየቀየሩና የተሻለ ነገር ለመሥራት እያጣሩ መሆኑን ተመልክቻለሁ፡፡ ‹‹አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ›› እንዳይሆን ሥጋት ስላለኝ፣ ጥንቃቄ የተመላበት ሥራ እንዲከናወን መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹አሸባሪ እኛ ነን›› ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ በእኔ እምነት ግን ሁሉም የኢሕአዴግ መንግሥት ሹመኞች አሸባሪ ባይሆኑም፣ ከላይ የጠቀስኳቸው ከሰባት የማይበልጡ አሸባሪዎች ነበሩ፡፡ እነዚህን የማፊያ አሸባሪ ቡድን አባላት በሕግ የሚያማክሩ አካላት ነበሩ፡፡ ክሱ ሁሉ የሕግ ቅባት እንዲኖርው የሚያደረጉ እነሱም እነማን እንደሆኑ በደንብ ይታወቃሉ፡፡ የእኛን ክስ ቀዶ የሰፋው የደኅንነት አማካሪ ማን እንደሆነ በግልጽ ይታወቃል፡፡ እኔን ‹‹በመንግሥት መኪና ሰዎች ደብረ ሊባኖስ ልከሃል›› በማለት ያላደረግኩትን አቀነባብሮ የከሰሰ አካል፣ የመንግሥትን መኪና ስብርብሩን በማውጣት በመንግሥት ገንዘብ እንዴት እንዳስጠገነ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ›› እንዳይሆን እንዲህ ዓይነቶቹን ገለለ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ካልሆነ የሚፈለገው የፍትሕ ሥርዓት አይመጣም፡፡ ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙትንም በፍጥነት ለፍርድ ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ መደላድሎች ከተሠሩ ለተአማኒ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ መደላድል መፍጠር ይቻላል፡፡ በኢሕአዴግም ውስጥ ከላይ እስከ ታች መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በእኔ እምነት ከአመራሩ ይልቅ አባሉ ቀድሞ ተለውጧል፡፡ ይኼንን የማይቀበለውን በክብር መሸኘት ነው፡፡ በተለይ ብአዴን በዚህ ላይ ጠንክሮ ሊሠራበት ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከማየውና ከምሰማው ኦሕዴድ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ የማይስማሙትን ቀደም ብሎ ያደረጉትን አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት በክብር ሸኝቶ ለውጡን ማስቀጠል ነው፡፡ ወደ አንድ ፓርቲ የመቀየር ጥናት ከተጀመረ ዓመታት ስለተቆጠረ ቶሎ አፋጥኖ ወደ ትግበራ መገባት አለበት፡፡ የኢሕአዴግ ጉባዔ በቅርቡ እንደሚካሄድ ሰምቻለሁ፡፡ በእኔ እምነት ሕገ ደንቡን አሻሽለው እስከ ምርጫው ጊዜ ቢያራዝሙት ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም የሰከነ ነገር በአመራሩ ውስጥ መስፈን አለበት፡፡ አለበለዚያ ለውጡን የማይፈልጉ ጉባዔውን ጠብቀው የሆነ ነገር ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ ይኼ የተለመደ የፖለቲካ ቁማር ነው፡፡ ለውጡ እንዳይደናቀፍ ሕጉ በሚፈቅደው ሁኔታ ነገሮችን ማየት ተገቢ ነው፡፡ ሌላው ሁሉንም ነገር ወደ ዳቦ ለመቀየር ሥራዎችን መሬት ማስያዝና በልማቱ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ግጭትንም ለማስወገድ ያለ ልክ የሆነን ሀብትን ወይም ድህነትን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ እኩልነትንና እኩል ተጠቃሚነትን በኢኮኖሚ መስኩም ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከልሶ ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ በውጭ ምንዛሪም ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አንድ ኤክስፖርትን በተመለከተ የሚገርመኝ ነገር፣ የአገሪቱ ኤክስፖርት ሁለት ቢሊዮን ዶላር የገባው 1998 .. ነው፡፡ ያኔ የኤክስፖርት ኮሚቴውን የሚመሩት አቶ መለስ ሻምፓኝ ከፍተውልኛል፡፡ እስካሁን ያለው ግን እዚያው ላይ ነው፡፡ ሁሉም አሁን የሚቀርቡት ችግሮች በፊት የነበሩ ናቸውና መሠረታዊ የሆነ ሥራ ይፈልጋል፡፡ በፋይናንስና በባንኪንግ ዘርፉ ላይ እውቀት ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ በጡረታ የተገለሉትን ጨምሮ በማማከር መጠቀሙ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ሕዝቡም ለውጡን መደገፍና ሊያደናቅፉ የሚመጡትን መመከትና መጠበቅ አለበት፡፡ ተቃዋሚዎችም ለውጡን ለመጠቀም በሰላማዊ ትግል መቀጠል አለባቸው፡፡ የተሠራውን እየደገፉና የቀረውን አብረው እየሠሩ ሰላሙን ማጠናከር አለባቸው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ከኢሕአዴግ የመጣ ለውጥ የትም አያደርስም ይላሉ፡፡ ለውጡ ከውስጥም ከውጭም ሊመጣ ይችላል፡፡ ዋናው መለኪያ ግን የሕዝብን ጥያቄ የሚመልስ ነው ወይ? የሚል መሆን አለበት፡፡ ሰከን ብሎ ማየትና ማመዛዘን ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ሰዎችን በብሔር ለይቶ ማጥቃት ተገቢ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም አገር ናት፡፡ ሁሉም ዘንድ በመጠንና በዓይነት ይለይ እንጂ አጥፊ ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ አጥፊውን ለይቶ ከማኅበረሰቡ ነጥሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የእከሌ ብሔር ጎድቶሃል፣ ደፍሮሃል ማለትን በመተው ቆም ብሎ ማሰብና መስከን ያስፈልጋል፡፡ ይኼ መንግሥት በአንድ ጊዜ ለውጥ ያመጣል ብሎ ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡ ጊዜ ሰጥቶና ተባብሮ በመሥራት ለውጡን ማምጣት ይገባል፡፡ በመጨረሻ ለሁሉም የሚጠቅመው የሕግ የበላይነትን ማክበር ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ‹‹ሕግን ገድለን እኛ ነፃ ከምንሆን፣ እኛ ሞተን አገር ነፃ ትውጣ›› ይላሉ፡፡ ይኼ ማለት በእኔ አረዳድ ሁሉም ያጠፋው ጥፋት ይፋ ወጥቶ፣ ይቅርታ ሰጪውና ይቅርታ ተቀባዩ ግልጽ ሆኖ በይቅርታና በመተማመን ቢፈታ መልካም ነው ለማለት ነው፡፡ ይቅርታ የማይጠይቁና ለውጡን የሚያደናቅፉ በሕግ ቢጠየቁ ተገቢ ነው፡፡ የሚደረገው እንቅስቃሴ ዕልቂትን ከሚጋብዝ በስተቀር ይኼንን የለውጥ ማዕበል ወደኋላ መመለስ አይችልም፡፡ ውጤቱ ‹‹መከራ፣ ስቃይ፣ ግፍ በቃን›› ብሎ በተነሳው ሕዝብ በመሆኑ በክፋት ተወልደው በክፋት ያደጉትን ሴራ ጠንሳሾችን ቀረብ ብሎ መምከር የተሻለ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡-  20 ዓመታት መለያየት በኋላ ኢትዮጵያና ኤርትራ ዕርቅ ፈጽመው ሰላም እየታየ ነው፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

አቶ መላኩ፡- ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በክልሎች መካከልም ሆነ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሕዝብ ጥላቻ የለም፡፡ ሕዝቡ ውስጥ ፍቅር፣ መተሳሰብና ሰላም ነው ያለው፡፡ በሁለቱም አገሮች ያለ ሕዝብ መሪዎቹን እንደሚቀበል ዓይተነዋል፡፡ አመራሮች የሚፈጥሩት ችግር እንጂ ሕዝቡ ፍቅር ነው፡፡ በመሆኑም አመራሮች የነበረባቸውን ችግር ተረድተውና ፈትተው ወደነበረበት መመለሳቸው አንድ ዕርምጃ ነው፡፡ በእኔ እምነት ተደጋግፈን አብረን ከኖርን አብረን ትልቅ እንሆናለን፡፡ ያለፉትን ቂም በቀልና ጥላቻ መተውና ዕድሉን ለሕዝብ መስጠት ነው፡፡ ሁለቱን አገሮች እስከ ውህደት ለማድረስ መንግሥታቱ መሥራት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡-  የጤናዎን ሁኔታ በመታሰርዎ ምክንያት ባለመከታተልዎ ሕመሙ  ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን ሲገልጹ ነበር፡፡ ሕመምዎ ምንድነው? ሕክምና እያገኙ ነው?

አቶ መላኩ፡- ሕመሜ ጨጓራ ነው፡፡ ቆስሎ መድማት ጀምሯል፡፡ በውጭ አገር ሕክምና ለማግኘት በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ማመሥገን ያለብኝን ላመሠግን እወዳለሁ፡፡ በዋነኛነት ፈጣሪዬን አመሠግናለሁ፡፡ በመቀጠል ሕዝቡን ላመሠግን እወዳለሁ፡፡ ሕዝቡ ዳኝነቱን ሰጥቶኛል፡፡ ባለቤቴን፣ ቤተሰቦቼንና ልጆቼንም አመሠግናለሁ፡፡ ከነበርኩበት ቤት በክረምት ወቅት ባለቤቴ ልጆች ይዛ እንድትወጣ ሲያደርጓት፣ ሼክ መሐመድ አል አሙዲና አቶ አብነት ገብረ መስቀል ቤት ተከራይተው እንዲቆዩ አድርገውልኛልና ዕድሜ ይስጥልኝ፡፡ የጊብሰን አካዳሚ ባለቤትም መታሰሬን ሰምተው ልጆቼን በነፃ ሲያስተምሩ በመቆየታቸው እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ ከተፈታሁም በኋላ የጎንደር ማኅበረሰብ ገንዘብ አዋጥተው በእግሬ እንዳልሄድ ተሽከርካሪ ገዝተው ስለሰጡኝ በጣም አመሠግናለሁ፡፡ የጤናዬን ሁኔታ የተመለከቱ ወገኖች ገንዘብ ማሰባሰብ ሲጀምሩ አብረውኝ ታስረው የነበሩት አቶ ከተማ ከበደ ‹‹ወጪውን ሙሉ በሙሉ የምችለው እኔ ነኝ›› በማለት የሕክምና ወጪዬን ስለሸፈኑልኝ እጅግ አድርጌ አመሠግናለሁ፡፡ ጠበቆቼንና የመገናኛ ብዙኃንን፣ ‹‹በእሱ ላይ አንመሰክርም›› በማለት ብዙ ሥቃይ ያዩትንና እውነቱን ሲያውቁ የታገሉልኝን የብአዴን አባላት ሁሉንም አመሠግናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከሕክምና በኋላ በምን ዓይነት የሥራ መስክ ለመሰማራት አስበዋል?

አቶ መላኩ፡- በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም የማገኛቸው ሁሉ ሕዝብን ማገልገል እንዳለብኝ እየነገሩኝ ነው፡፡ ጥቂቶቹ ስላንገላቱኝ፣ ስላሰቃዩኝና ጥቃት ስላደረሱብኝ አገሬን አልጠላም፡፡ ሕዝቤንም እወዳለሁ እንጂ ምንም ዓይነት ቅያሜ ውስጥ አልገባም፡፡ አገሬን ጥዬ የትም አልሄድም፡፡ ሕይወቴ እስካለ ድረስ አገሬን አገለግላለሁ፡፡ አሁን ያለውን ለውጥ ለማገዝ ዝግጁ ነኝ፡፡ እንዴት ለሚለው እግዚአብሔር በመራኝ ነው፡፡ ይኼ ነው ባልልም ለማገልገል ግን ዝግጁ ነኝ፡፡

No comments:

Post a Comment