ታሪክ
“ባንዶቹ”
(ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቡድኖች)
.
በሳይም ኦስማን
.
(ራስ ባንድ)
.
ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ‘ወርቃማ ዘመን’ ስናወራ እነዚያን መሳጭ ሙዚቃዎች ከዘፋኞች ኋላ ሆነው ስላቀነባበሩት ስለ ባንዶቹ ሳናነሳ አናልፍም። በዚህ ጽሑፍ (እና በቀጣዮቹ ክፍሎች) የዋና ዋናዎቹን ዘመናዊ ባንዶች ታሪክ እና ባንዶቹን ስላቋቋሙት ሙዚቀኞች አጠር አድርጌ አቀርባለሁ።
በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ በጣም ተወዳጅ የነበሩት የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ፣ የፖሊስ ባንድ፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ኦርኬስትራ፣ እና የምድር ጦር ኦርኬስትራ ነበሩ። በ1953 ዓ.ም የታህሳሱ ግርግር የኃይለሥላሴን መንግስት ለመገልበጥ የተሞከረበት ጊዜ፣ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ሁለተኛ ምዕራፍን ከፈተ። በዚህም ወቅት የክቡር ዘበኛ ኦኬስትራ ለበርካታ ወራት ለመበተን በቃ። ብዙዎቹ አባላቶቹም ከኦኬስትራው እየለቀቁ ሌሎች የሙዚቃ ቡድኖችን (ፖሊስ፣ ምድር ጦር እና ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ቴያትር) መቀላቀል ጀመሩ። እነዚህ ዋና ዋናዎቹ ኦኬስትራዎች ቀስ በቀስ ወደ ብዙ ትናንሽ ባንዶች እየተቀየሩ መጡ።
እነዚህም ትናንሽ ባንዶች መጀመሪያ ስራ የጀመሩት በተለያዩ የአዲስ አበባ ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ ነበር። ለዚህም ይመስላል የባንድ ስማቸውን በሆቴሎቹ ስም ያደረጉት … እንደ “ራስ ባንድ”፣ “ግዮን ባንድ”፣ “ሸበሌ ባንድ” የመሳሰሉት። ብዙም ሳይቆይ ሆቴሎቹ በጣም ታዋቂ መዝናኛ ቦታዎች እየሆኑ መጡ። በተለይም አርብ ማታ እነዚህን የሙዚቃ ድግሶች ለመታደም የማይቀርበት ቦታ ሆኑ።
ራስ ሆቴል በ1950ዎቹ መባቻ።
.ራስ ባንድ
.
የየመጀመሪያው ራስ ባንድ የተቋቋመው በ1953 ዓ. ም ነበር። ባንዱንም የመሠረቱት ተፈራ መኮንን (ፒያኖ)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክስፎን)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ባህሩ ተድላ (ድረምስ)፣ ባህታ ገብረሕይወት (አማርኛና ትግርኛ ድምፃዊ)፣ ግርማ በየነ (እንግሊዘኛ ድምፃዊ) እና ገብረአብ ተፈሪ (አስተናባሪና ገጣሚ) በመሆን ነበር። በዛሬ ዘመን በሕይወት በመሀከላችን የሚገኙት ጌታቸው ወልደሥላሴ፣ ባህታ ገብረሕይወት እና ግርማ በየነ ናቸው።
ራስ ባንድ በራስ ሆቴል (1953-1956 ዓ.ም)። [ከግራ ወደ ቀኝ]፤ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ባህሩ ተድላ (ድራም)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክሰፎን)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ግርማ በየነ (ማራካስ/ፐርከሽን) … |ምስል 1|
የራስ ባንድ አባላት አብዛኛዎቹ ነርሲስ ናልባዲያን ባሰለጠነው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ኦኬስትራ ውስጥ ይጫወቱ የነበሩ ናቸው። እነዚህም ተፈራ መኰንን፣ ጥላሁን ይመር፣ እና ባህሩ ተድላ
የራስ ባንድ አባላት አብዛኛዎቹ ነርሲስ ናልባዲያን ባሰለጠነው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ኦኬስትራ ውስጥ ይጫወቱ የነበሩ ናቸው። እነዚህም ተፈራ መኰንን፣ ጥላሁን ይመር፣ እና ባህሩ ተድላ ናቸው። እስከ 1947 ዓ.ም. ድረስም ሶስቱ አባላት የክቡር ዘበኛ የጃዝ ሲንፈኒ ኦኬስትራ ውስጥ በፍራንዝ ዜልወከር ሥር ተምረው ነበር። በክቡር ዘበኛ ኦሮኬስትራ ውስጥ ተፈራ መኰንን ቤዝ ሲጫወት ጥላሁን ይመር እና ባህሩ ተድላ ደግሞ ድራም ተጫዋቾች ነበሩ። በ1953 ዓ.ም አጋማሽም የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሲበተን ተጨማሪ ሙዚቀኞችን (ጌታቸው ወልደሥላሴ እና ዘውዱ ለገሰ) እና ሁለት ድምፃውያንን ይዘው ወደ ራስ ሆቴል አመሩ።
የራስ ባንድ አባላት አብዛኛዎቹ ነርሲስ ናልባዲያን ባሰለጠነው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ኦኬስትራ ውስጥ ይጫወቱ የነበሩ ናቸው። እነዚህም ተፈራ መኰንን፣ ጥላሁን ይመር፣ እና ባህሩ ተድላ ናቸው። እስከ 1947 ዓ.ም. ድረስም ሶስቱ አባላት የክቡር ዘበኛ የጃዝ ሲንፈኒ ኦኬስትራ ውስጥ በፍራንዝ ዜልወከር ሥር ተምረው ነበር። በክቡር ዘበኛ ኦሮኬስትራ ውስጥ ተፈራ መኰንን ቤዝ ሲጫወት ጥላሁን ይመር እና ባህሩ ተድላ ደግሞ ድራም ተጫዋቾች ነበሩ። በ1953 ዓ.ም አጋማሽም የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሲበተን ተጨማሪ ሙዚቀኞችን (ጌታቸው ወልደሥላሴ እና ዘውዱ ለገሰ) እና ሁለት ድምፃውያንን ይዘው ወደ ራስ ሆቴል አመሩ።
“አርብ ማታ በራስ ሆቴል የሚያስደስት ጊዜ ነበር” ይላል ባህታ ገብረሕይወት – Addis Live ራዲዮ ኢንተርቪው ላይ፣ ባህታ የሆቴሉን ድባብ ሲያስታውስ ሁሉም የባንዱ አባላት በሚገባ ዘንጠው መገኘት ነበረባቸው። እያንዳንዱም የሆቴል ተጠቃሚ አለባበሱን አስተካክሎ መገኘት የሆቴሉ ህግ ነበር። በሚገባ አለባበሱ አልተስተካከለም ብለው ለሚያስቡት ተጠቃሚ ክራቫት ይሰጠው ነበር። ብቻቸውን የሚመጡ ተስተናጋጆች እምብዛም ናቸው። ሁሉም ጥንድ ጥንድ ሆኖ ይደንስ ነበር።
ራስ ባንድ በአክሱም አዳራሽ መክፈቻ በዓል (ታኅሣስ 4፣ 1956 ዓ.ም)። [ከግራ ወደ ቀኝ]፤ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክሰፎን)፣ ባህሩ ተድላ (ድራም)፣ ባህታ ገብረሕይወት (ድምፅ)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ግርማ በየነ (ማራካስ/ፐርከሽን) … |ምስል 2|
ራስ ባንድ ውስጥ እያለ ነበር ባህታ ብዙዎቹን ስራዎቹን ያበረከተልን። እነ “አንቺም እንደ ሌላ”፣ “ደግሞ እንደምን አለሽ”/“ካላጣሽው አካል”፣ “ስቃይ ዝክኣል’ዩ”፣ “የጥላቻ ወሬ”፣ “ያ ያ” እና “ወደ ሀረር ጉዞ” የመሳሰሉትን።
[“ካላጣሽው አካል”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ (የቀድሞ ራስ ባንድ አባላት)። 1957-1960 ዓ.ም።]
ባህታ የትግርኛ ዘፈኖቹን ግጥም የጻፈው እራሱ ሲሆን፣ ብዙዎቹን የአማርኛ ዘፈኖች ግጥም ደግሞ ገብረአብ ተፈሪ ነበር የሚጽፋቸው። ሙዚቃዎቹን የሚጽፈውና የሚያቀናብረው ፒያኖ ተጫዋቹ ተፈራ መኰንን ነበር። ባህታም በዚህ ዘመን ከጻፋቸው ሙዚቃዎች ዜማ አንዱ እና ግርማ በየነን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ታዋቂ ያደረገው ዘፈን ‘ይበቃኛል’ የተሰኘው ነበር።
በዚሁ ራስ ባንድ በሚሰራበት ጊዜም ነበር ባህታ በትርፍ ጊዜው ተምሮ አካውንቲንግ ያጠናው። በ1964 ዓ.ም ከሙዚቃ ዓለም ሲርቅ ለግዮን ሆቴል እና ለፊልም ኮርፖሬሽን የሂሳብ ሰራተኛ ሆኖ ይሰራ ነበር። ባህታ እንደሚለው የኢትዮጵያ ሙዚቃ አካሄድ አላምር ብሎት ነበር ከሙዚቃ አለም የራቀው። በታህሳስ 1996 ዓ.ም ከብዙ አመታት በኋላ ባህታ ገብረሕይወት ‘አንቺም እንደሌላ’ን Either Orchestra ከሚባል ቦስተን ከሚገኝ የጃዝ ቡድን ጋር አቅርቦ ነበር።
[“አንቺም እንደሌላ”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን/ራስ ባንድ)። 1957-1960 ዓ.ም።]
የመጀመሪያው የራስ ባንድ የተመሰረተው ከ1953 ዓ.ም ነበር። ታዲያ በ1956 ዓ.ም አጋማሽ ሁለቱ የባንዱ አባላት (ጌታቸው ወልደሥላሴ እና ዘውዱ ለገሰ) በሌሎች ሙዚቀኛች የተተኩ ይመስላል። ወዳጄነህ ፍልፍሉ ከዚህ ወቅት ጀምሮ ሳክሰፎን በመያዝ፣ አሰፋ ባይሳ ደግሞ ትራምፔት በመጫወት ራስ ባንድን ተቀላቀሉ። በሐምሌ 1956 ዓ.ም አካባቢም እንግሊዘኛ ድምፃዊው ግርማ በየነ ራስ ባንድን ለቀቀ። ብዙም ሳይቆይ በ1957 ዓ.ም የባንዱ አባላት ከራስ ሆቴል ወጥተው በግዮን ሆቴል ለተወሰኑ ዓመታት “ግዮን ባንድ” ተሰኝተው ተጫውተዋል።
ራስ ባንድ በነሐሴ 1956 ዓ.ም። [ከግራ ወደ ቀኝ] ባህሩ ተድላ (ድረምስ)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ አሰፋ ባይሳ (ትራምፔት)፣ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ባሕታ ገብረሕይወት (ድምፃዊ)፣ እና ወዳጄነህ ፍልፍሉ (ሳክሰፎን)። |ምስል 3|
በድምፃዊነት እና በፐርከሽን ከሦስት ዓመት በላይ “ራስ ባንድ” ከተጫወተ በኋላ ግን ወጣቱ ግርማ በየነ በተራው የራሱን ባንድ ለማቋቋም ወሰነ።
ግርማ በየነ በ1956 ዓ.ም መገባደጃ። |ምስል 4|
ግርማ በየነ በአዲስ አበባ ከተማ ተወልዶ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም በዛው በካቴድራል ት/ቤት በሚከታተልበት ወቅት ነበር የሙዚቃ ፍቅር ሥር የሰደደበት። ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ለጊዜው ተቀጥሮ በመድረክ በድምፃዊነት መቅረብ ጀመረ። የማዜም እና የመዝፈን ፍቅሩም ሲብስበት በ1953 ዓ.ም ትምህርቱን ከልዑል መኰንን ት/ቤት አቋርጦ ከታኅሣስ ግርግር በኋላ የተመሰረተውን “ራስ ባንድ” በምዕራባዊ ዘፈን አቀንቃኝነት ተወዳድሮ ተቀላቀለ።
ግርማ በራስ ባንድ ቆይታው ከእንግሊዝኛ ዘፈን አቀንቃኝቱ ባሻገር የሙዚቃ መሳሪያ ችሎታውን አዳበረ። በፐርከሽን መሳሪያዎች (ማራካስ እና ድራምስ) ጀምሮም ቀስ በቀስ ፒያኖ የመጫወት ልምድ አካበተ። ከሦስት አመት ተኩል ቆይታ በኋላም በሐምሌ 1956 ዓ.ም ራስ ባንድን በራሱ ፈቃድ ለመልቀቅ ወሰነ።
ግርማ ለተወሰኑ ወራት በተለያዩ የአዲስ አበባ ምሽት ክበቦች (እነ La Mascotte እና Domino Club) ከግርማ ዘማርያም (ድራምስ) ጋር ፒያኖ እየተጫወተ መዝፈኑን ተያያዘው። በሁለቱ ግርማዎች የተቋቋመውን ባንድ “The Girmas” በመባል ይጠራ ነበር።
Audio Player
00:00
00:00
[“ትወጅኝ
እንደው”። ግርማ በየነ እና ግርማ ዘማርያም።
(ዜማ/ግጥም) ግርማ በየነ።
The Girmas።
1957 ዓ.ም።]
.
ይህም ባንድ ቁጥሩን በርከት በማድረግ ጌታቸው ደገፉ (ኦርጋን)፣ ኃይሉ “ዝሆን” ከበደ (ቤዝ)፣ ተስፋማርያም ኪዳኔ (ቴነር ሳክስ) እና ፈለቀ ነጋሽን (ትራምፔት) ወደ ቡድኑ ጨመረ። በጊዜው ከተጫወቷቸው ዜማዎች መሀከልም “ትወጅኝ እንደው”/“ቁርጡን ንገሪኝ”፣ “ጥሩልኝ ቶሎ”/“ፍፁም ፍፁም” እና “ሮኬት ቢሰራ”/“እቅጩን ንገሪኝ” ይጠቀሳሉ።
Audio Player
00:00
00:00
[“ሮኬት ቢሰራ”። ግርማ በየነ። (ዜማ) Sam Cooke። The Girmas/ራስ ባንድ። 1957 ዓ.ም።]
.
ከጥቂት ጊዜም በኋላ የቀድሞው “ራስ ባንድ” ወደ ግዮን ሆቴል በ1957 ዓ.ም ሲዛወር ግርማ በየነ በተራው ሁለተኛውን “ራስ ባንድ“ በዚያው በራስ ሆቴል አቋቋመ። ይህም ባንድ ለአምስት ዓመታት ያህል በርካታ ሥራዎችን በአዲስ አበባ ራስ ሆቴል ሲያቀርብ ቆየ። በዚህኛውም ራስ ባንድ ውስጥ የነበሩት ግርማ በየነ (ፒያኖ እና እንግሊዘኛ ዘፈን)፣ ግርማ ዘማርያም (ድራምስ)፣ ኃይሉ “ዝሆን” ከበደ (ቤዝ)፣ ተስፋማርያም ኪዳኔ (ቴነር ሳክሰፎን)፣ ፈለቀ ነጋሽ (ትራምፔት) እንዲሁም ሁለቱ ድምፃውያን ምኒልክ ወስናቸው እና ሰይፉ ዮሐንስ ነበሩ።
ሁለተኛው
ራስ
ባንድ
በ1960
ዓ.ም መገባደጃ።
[ከግራ
ወደ
ቀኝ]
ግርማ
ዘማርያም (ድራምስ)፥ ምኒልክ ወስናቸው (ድምፅ)፥ ግርማ በየነ (ፒያኖ/ድምፅ)፥ ሰይፉ ዮሐንስ (ድምፅ)፥ ኃይሉ “ዝሆን” ከበደ (ቤዝ) እና ተስፋማርያም ኪዳኔ (ቴነር ሳክሰፎን)
ኃይሉ “ዝሆን” ከበደ ከቅፅል ስሙ መረዳት እንደሚቻለው ሰውነቱ ግዙፍ ነበረ። ኃይሉ በግሩም ቤዝ ተጫዋችነቱ ከራስ ባንድ አባልነቱ ባሻገር በ1960ዎቹ ከግርማ በየነ ጋር በAll-Stars Band እና ዓለም-ግርማ ባንዶች ውስጥ አባል ሆኖ ነበር። ለተወሰነ ጊዜም በዝነኛው Soul Ekos ባንድ ተጫውቷል። ከአብዮቱ በኋላም በሀገር ፍቅር ማህበር በሙዚቀኝነት አገልግሏል።
ተስፋማርያም ኪዳኔ ተወልዶ ያደገው ኤርትራ ውስጥ ነው። ተስፋማርያም ሳክሰፎን መጫወት የጀመረው ከአሥመራ ፖሊስ ኦርኬስትራ ጋር ነበር። ሁለተኛው ራስ ባንድን ከተቀላቀለም በኋላም ከግርማ በየነ እና ኃይሉ ከበደ ጋር በመሆን All-Star ባንድ ውስጥ አብሮ ተጫውቷል።
አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ምኒልክ ወስናቸው የሙዚቃ ጅማሬው በ1951 ዓ.ም በተቀጠረበት ዝነኛው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴያትር ኦርኬስትራ ነበር። በዛም ብዙ ምርጥ ዘፈኖችን ዘፍኖ ነበር – እነ “ፍቅር በአስተርጓሚ”፣ “ፍቅር አያረጅም”፣ “ስኳር ስኳር” እና የመሳሰሉትን። ምኒልክ ራስ ባንድን በ1957 ዓ.ም ከተቀላቀለ በኋላም “ውብ ናት” እና ሌሎችን ግሩም ዘፈኖች ተጫውቶ ነበር። “ውብ ናት” ላይ በአጃቢነት የሚቀበለው ግርማ በየነ ነው።
Audio Player
00:00
00:00
[“ውብ ናት”። ምኒልክ ወስናቸው። (ዜማ) ምኒልክ ወስናቸው (ግጥም) ግርማ በየነ። ራስ ባንድ። 1957-1961 ዓ.ም።]
.
ወጣቱ ሰይፉ ዮሐንስም ከሁለተኛው ራስ ባንድ ጋር ለበርካታ ዓመታት ተጫውቶ ነበር። በዚህ ዘመን በጣም ከታወቁለት ሥራዎቹ መካከልም “ጽጌረዳ”፣ “ቆንጅትዬ”፣ “ሃና”፣ እና “መለወጥሽ ምነው” ናቸው። የሰይፉም ታላቅ እህት ተወዳጅዋ ዘፋኝ ራሔል ዮሐንስ ናት። ለሬድዮ ፋና አንድ ጊዜ በሰጠችው ቃለ ምልልስ፣ አባታቸው በሰይፉ ዘፋኝነት እጅግ ይበሳጭ እንደነበረና ልጄ አይደለህም ብሎ እስከመካድ ደርሶ በሽማግሌዎች ልመና ይቅርታ እንዳደረገለት ተናግራ ነበር።
ሰይፉ “ጽጌሬዳ”፣ “ቆንጅትዬ” እና “መለወጥሽ ምነው” የተሰኙትን የተጫወተው ሁለተኛው ራስ ባንድ ጋር ሳለ ሲሆን ድርሰቶቹን የጻፈውና ያቀናበረው ግርማ በየነ ነበር። ሰይፉ ከራስ ባንድ ቆይታውም በኋላ በየምሽት ክበቦቹ (ዙላ፣ ቬኑስ) በመጫወት ዝነኛው ሶውል ኤኮስ (Soul Ekos) ባንድን ተቀላቀለ።
.
Audio Player
00:00
00:00
[“ቆንጂትዬ”። ሰይፉ ዮሐንስ። (ግጥም) ግርማ በየነ። ራስ ባንድ። 1957-1961 ዓ.ም።]
Audio Player
00:00
00:00
[“መለወጥሽ
ምነው”። ሰይፉ ዮሐንስ። (ዜማ/ግጥም) ግርማ በየነ። ራስ ባንድ። 1957-1961 ዓ.ም።]
.
ከነዚህ ሙዚቀኞች ባሻገርም፣ በተለይ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ፣ ከባሕር ማዶ የተመለሰው ወጣቱ ሙላቱ አስታጥቄ ባንዱን ተቀላቅሎ ከራስ ባንድ ጋር በአዲስ አበባ እና ሐረር ራስ ሆቴል መድረኮች ላይ ዛይሎፎን እና ኮንጐ ድራምስ ተጫውቷል።
.
ራስ ባንድ በ1961 ዓ.ም መባቻ።
[ከግራ
ወደ
ቀኝ]
ግርማ
በየነ
(ፒያኖ)፣ ተስፋማርያም
ኪዳኔ
(ቴነር
ሳክሰፎን)፣ ሙላቱ አስታጥቄ (ዛይሎፎን/ኮንጎ ድራምስ)፣ ኃይሉ ከበደ (ቤዝ ጊታር/ኰንትሮ ባስ)፣ ፈለቀ ኪዳኔ (ትራምፔት)፣ ግርማ ዘማርያም (ጃዝ ድራምስ)
.
በመጨረሻም፣ ዝነኛው ራስ ባንድ በ1961 ዓ.ም (በመበታተኑ ዋዜማ እና መባቻ) በአምኃ እሸቴ “ሐራምቤ ሙዚቃ ቤት“ አሳታሚነት የግርማ በየነ፣ ሙላቱ አስታጥቄ እና ዓለማየሁ እሸቴን ሙዚቃዎች በሸክላ ለማስቀረጽ ችሎ ነበር።
.
Audio Player
00:00
00:00
[“ያ ታራ!”። ዓለማየሁ እሸቴ። ራስ ባንድ። 1961 ዓ.ም።]
.
Audio Player
00:00
00:00
[“ይበቃኛል”። ግርማ በየነ። (ግጥም/ዜማ) ባሕታ ገ/ሕይወት። ራስ ባንድ። 1961 ዓ.ም።]
No comments:
Post a Comment