Monday, July 9, 2018

በሰኔ ወር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከተከናወኑና ድርጊቶች መካከል ጥቂቶቹ


 
🔯🔯🔯
). የንጉሰ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የጀኔቫ ንግግር
ንጉሰ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራን ለዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) ተወካዮች ያሳወቁት 82 ዓመታት በፊት (ሰኔ 23 ቀን 1928 .) ነበር፡፡
...

ንጉሰ ነገሥቱ ጀኔቫ (ስዊዘርላንድ) በሚገኘው የመንግሥታቱ ማኅበር ተወካዮች ፊት ቀርበው የፋሺስት ወረራ የአገራቸውን ሉዓላዊነት የደፈረ ተግባር እንደሆነ በአማርኛ ቋንቋ አስረድተዋል፡፡ በወቅቱም ወደ ስብሰባ አዳራሹ ገብተው የነበሩ የኢጣሊያ ጋዜጠኞችን የንጉሰ ነገሥቱን ንግግር በጩኸትና በጭብጨባ ለማቋረጥ ሙከራ አድርገው ነበር፡፡
🔯🔯🔯
). የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ እረፍት
ደራሲ፣ ሀኪምና የምጣኔ ሀብት ጥናት ባለሙያ የነበሩት ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ያረፉት 99 ዓመታት በፊት (ሰኔ 24 ቀን 1911 .) ነበር፡፡
...
ነጋድራስ /ሕይወት የተወለዱት ታሪካዊቷ ዓድዋ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወደኋላ መቅረት አሳስቧቸው ከእድሜያቸው በላይ የደከሙ ምሁር ናቸው፡፡ ‹‹አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ›› እና ‹‹መንግሥትና ሕዝብ አስተዳደር›› በተሰኙት መጽሐፎቻቸው እንኳን ያን ጊዜ ዛሬም ከምሁራኖቻችን በማንጠብቀው ደግነትና ብስለት የተሞላበት ትንተናና በቀላል ቋንቋ ለአገራቸው የሚመኙትን የእድገት ሃሳቦችን ያሰፈሩ ቁንጮ ምሁር ናቸው፡፡
...
ነጋድራስ /ሕይወት ወደ ጀርመንና ኦስትሪያ በመሄድ የሕክምና ትምህርት አጥንተዋል፡፡ በዓፄ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት ፀሐፊ በመሆን ሠርተዋል። የድሬዳዋ ጉምሩክ ኃላፊም ሆነው ተመድበው አገልግለዋል፡፡
...
[ስለነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ወደፊት ብዙ የምንወያየው ነገር ይኖረናል!]
🔯🔯🔯
). የአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ እረፍት
የቅኔ፣ የትርጓሜና የቋንቋ ሊቅ የነበሩት አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ያረፉት 74 ዓመታት በፊት (ሰኔ 24 ቀን 1936 .) ነበር፡፡
አለቃ ኪዳነወልድ የተወለዱት ሸዋ ውስጥ ነው፡፡ ለትምህርት ሲደርሱ በአካባቢያቸው የነበረውን የአገራቸውን ትምህርት ተማሩ።
...
በኋላም ወደ ጎንደር ተጉዘው የመጻሕፍትን ትርጓሜ አጠኑ። በጊዜው በነበራቸው የቀለም አቀባበል፣ የሚስጥር መመራመርና መራቀቅ ምክንያት በጉባኤው ላይ «የቀለም ቀንድ» የሚል ቅጽል ተሰጣቸው።
...
በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) ጥሪ መሰረት ከሚኖሩበት ኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሕዝቅኤልን ንባቡን ከነሙሉ ትርጓሜው ጋር አሳትመው ማስረከባቸውን ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የመጀመሪያውን መዝገበ ፊደል አውጥተው ከልዩልዩ ቋንቋዎች ጋር በማመሳከር አሳትመዋል፡፡ መፅሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ የተባለውን የግዕዝና የአማርኛ መዝገበ ቃላት ስራ የጀመሩትም እርሳቸው ነበሩ፡፡
...
አለቃ ኪዳነወልድ የኢትዮጵያ ፊደል አመጣጡንና ባህሉን በውል አስተባብረው በማቅረባቸውም በጊዜው ተቋቁመው ለነበሩት ትምህርት ቤቶች መመሪያና መማሪያ ለመሆን በቅተዋል።
ቀጥለውም ትንሽ አማርኛ ፊደል ከአረብና ከዕብራይስጥ አቆራኝተው አሳትመዋል። በተለያየ ዘይቤ ያቀርቧቸው የነበሩት ግጥሞች ለትውልድ ታላቅ ጥቅም ይሰጣሉ ተብለው የሚገመቱ ናቸው።
...
በአጠቃላይ አለቃ ኪዳነወልድ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ እድገት ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰው ነበሩ። አለቃ ኪዳነወልድ ከግዕዝና ከአማርኛ በተጨማሪ አረብኛ፣ ዕብራይስጥ እና የላቲን ቋንቋዎችን አጠናቅቀው ያውቁ ነበር። ሰኔ 24 ቀን 1936 . አርፈው ደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ።
🔯🔯🔯
). የራስ ጉበና ዳጬ (አባ ጥጉ) እረፍት
የታላቁ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ ቀኝ እጅና ታማኝ የነበሩት ራስ ጎበና ዳጬ (አባ ጥጉ) ያረፉት 129 ዓመታት በፊት (ሰኔ 27 ቀን 1881 .) ነበር፡፡
...
ራስ ጎበና ልጅ ምኒልክ ከመቅደላ አምልጠው ሸዋ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በአገር ማቅናት ስራው ላይ የላቀ ተሳትፎ የነበራቸው የጦር መሪ ነበሩ፡፡ ራስ ጎበና ከራስ ዳርጌ ሳሕለሥላሴ ጋር በመሆን ‹‹ራስ››ነት ማዕረግን ከምኒልክ ዘንድ የተቀበሉ የመጀመሪያ ሰው ነበሩ፡፡ የራስ ጎበና ጀግንነት በየአገሩ የታወቀ ነበር፡፡ በዚህም በዘመኑ ‹‹በትግሬ አሉላ፣ በሸዋ ጎበና፣ በጎጃም ደረሶ›› እየተባሉ ዝናቸው ከዳር እስከዳር ይወራ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡
...
ራስ ጎበና ተከብረውና ተፈርተው ሲኖሩ ቆይተው ሰኔ 27 ቀን 1881 . አረፉ፡፡ ስርዓተ ቀብራቸውም በደብረ ሊባኖስ ተፈፀመ፡፡ ከሞታቸው በኋላም ጋሻቸው ለኡራኤል ቤተ-ክርስቲያን ተስጥቶ ነበርና እንዲህ ተብሎ ተገጠመ
‹‹የሚሰጡት ቢያጡ ከድፍን ሐበሻ፣
ለኡራኤል ሰጡት የጎበናን ጋሻ››
...
የራስ ጎበና ዳጬ ልጅ ወይዘሮ አስካለ ጎበና የስመጥሩ አርበኛ የራስ አበበ አረጋይ ባለቤት ነበሩ፡


No comments:

Post a Comment