Thursday, August 16, 2018

የገበያ ዳኛ እና መርካቶ


ዛሬ ላይ ከኒዮርክና ብራስልስ ቀጥላ የበርካታ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መቀመጫ የሃገረ ኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና ብቻ ሳትሆን የኢኮኖሚውም ማዕከል ነች አዲስ አበባ፡፡ ከተመሰረተችበት እለት አንስቶ በርካታ ታሪካዊ ሂደቶችን አሳልፋለች፡፡ ገና በልጅነቷ ወቅት ከነበሯት አይረሴ ትዝታዎች መሃከል የግብይት እንቅስቃሴዋና የገበያ ዳኛ አንዱ ነው፡፡
በዛሬ መሰናዷችንም ይሄንን ጉዞዋን ልናስቃኛችሁ ወደናል፡፡ አብረራችሁን ቆዩ፡፡

ከጠዋትጀምሮ ከአዲስ አበባና አካባቢዋ ገበያተኞች ወደ ገበያ ይወጣሉ፡፡ ምንም ዓይነት ሱቅም ሆነ በረንዳ የለም ብቻ እንዲያው ባዶ ሜዳ ላይ ነጠላቸውን ዘርግተው እቃዎቻቸውን ይዘረግፉና ይገበያያሉ፡፡ሁሉም የራሱ የሆነ የተወሰነ ቦታ አለው፡፡ ጨርቅ ተራ ፣እህል ተራ እንጨት ተራ ከብት ተራ አልጋ ተራ ወዘተእየተባባለ ተከፋፍሏል፡፡
በእንዲህ አይነት ገበያዎች በምንም ታምር የገበያ ዳኛ መቅረት የለበትም፡፡ በገበያተኞች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ሁለቱንም ወገን በሚያስማማ መልኩ የሚዳኝ ዳኛ መኖር አለበት፡፡ እንዲህ አይነት ዳኝነቶች በአውላላ ሜዳ ላይ ይካሄዳሉ፡፡

በገበያው ውስጥ ብትን ጨርቆች የሚለኩት በክንድ ነው፡፡ አንድ ቀን ታድያ ሁለት ገበያተኞች ይጨቃጨቃሉ፡፡ ጨርቁን የሚገዛው ሰውዬ እጅግ በጣም ረጅም ሲሆን ሻጩ ደግሞ በጣም አጭር ነው፡፡ እናም ገዥ በሚችለው መልኩ ክንዱን ዘርግቶ ጣቶቹን ወጥሮ አስር ክንድ ለካና ምልክት አደረገ፡፡ ሻጩ ደግሞ በሚችለው ሁሉ ጣቶቹን ሳይወጥር እሱም አስር ክንድ ለካና ምልክት አደረገ፡፡ ሁለቱም በለኩት መካከል ከአነነድ ክንድ የሚበልጥ ልዩነት መጣ፡፡ ገዥው ሻጩን አውቆ ክንዱን ሳይወጥር ይለካል ሲል አመረረ፡፡ ሻጩ በምኒልክ እየማለ ሃቀኛ ነጋዴ መሆኑን እግዚአብሄርን ምስክርነት ጠራ፡፡ እናም መግባባት ባለመቻላቸው ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ዳኛ ፍለጋ መሄድ ብቻ ነበርና ጎን ለጎን ግራና ቀኝ እጆቻቸውን በነጠላቸው ጫፎች ሸብ አድርገው ከቋጠሩ በኋላ ወደ ገበያው ሸምጋይ ዳኛ በብዙወሬኞች ታጅበው ሄዱ፡፡ብቸኛው የገበያ ፈላጭ ቆራጭ ዳኛ ከፍ ብላ ከተሰራች አንዲት ባለሁለት ቆርቆሮ መደበር ላይ ተኮፍሶ ተቀምጧል፡፡
የሚንጫጫውን ወሬኛ ዝም ካስባለ በኋላ በትዕግስት ሁለቱንም ባለጉዳዬች አዳመጠ፡፡
ሁለቱም በእምዬ ምኒልክ እየማሉና እግዜሩን ምስክርነት እየጠሩ ችግራቸውን ለዳኛው አስረዱ፡፡ ገዥም ሻጭም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እየጮሁ ዳኛውን ለማሳመን ሞከሩ፡፡ ዳኛው ሁለቱንም በትዕግስት ካዳመጠ በኋላ ወደ ሁለቱ
ባለጉዳዮች እያየ መጀመርያ ገዥውን አስር ክንድ እንዲለካና ምልክት እንዲያደርግ አዘዘው፡፡ ወድያው ሻጩንም አስር ክንድ እንዲለካና ምልክት እንዲያደርግ አዘዘው፡፡ ሁለቱም ጨርቁን ለክተው ምልክት አድርገው እንደጨረሱ ዳኛው ጨርቁን ተቀብሎ ሁለቱም ምልክት ያደረጉበት ቦታ ላይ በመቀስ ቆረጠውና ፍርዱን ሲሰጥ ‹‹በእምዬ ምኒልክሁለታችሁም እውነት አላችሁ ግን እንዳትጣሉ›› በማለት ገዥው በሻጩ አጭር ክንድ መስማማት ስላለበት ነጋዴውም ከዚህ ትርፍ እንዳያገኝ ልዩነት ያመጣውን ጨርቅ ለዳኝነቱ ዋጋ አስቀርቶ ሁለቱን ባለጉዳዮች አሰናበታቸው፡፡
በዳኛው ፍርድ ሁሉም ተደስተዋል፡፡ ነጋዴው - ገዥው ሰውዬ በሱ አጭር ክንድ የተለካ ጨርቅ በመግዛቱና በረጅሙ ክንዱ ባለመጠቀሙ ገዥው ደግሞ - ነጋዴው ባለችው አጭር ክንድ እየለካ ከፍ ያለ ትርፍ ባለማግኘቱ ወሬኞችም ሳምንቱን
ሙሉ የሚያወሩት ወሬ በማግኘታቸው ዳኛውም ከጨርቋ በተጨማሪ ጥቂት ቤሳ ሳንቲሞች በመስራቱ ብቻ ሁሉም ተደስተው ዳኝነቱ ተበተነ፡፡
የንጉስ ሰሎሞንን ፍርድ የሚስተካከል ፍርድ ይልዎታል ይሄ ነው፡፡
(የሃበሻ ጀብዱ አዶልፍ ፓርለሳክ ፅፎት ተጫነ ጆብሬ እንደተረጎመው)


No comments:

Post a Comment