Thursday, August 16, 2018

የ"ይቻላል" መንፈስ የሰፈነበት የአዲስ አበባው ቴድኤክስ የንግግር መድረክ

የቴዴክስ አዲስ ተሳታፊዎች
ልጅ ሳለ ሰዎች በስልክ ሲነጋገሩ ያያል። 'እንዴት ድምጽ በቀጭን ሽቦ ይተላለፋል?' ሲል በጠያቂ አእምሮው ያሰላስላል። አውጥቶ አውርዶም ስልክ ለመፈልሰፍ ይወስናል።
ያስፈልጉኛል ያላቸውን እቃዎች ከአካባቢው መሰብሰብ ጀመረ። ጣሳን ለድምጽ መሳቢያነት ተጠቅሞ ከጭቃ የተሰራ የስልክ እጀታ ሠራ።
ስልክ የመጀመሪያ የፈጠራ ሙከራው አይደለም። ዘወትር አዳዲስ ነገር ስለመፈልሰፍ ከማሰብ ወደ ኋላ አይልም። እስራኤል ቤለማ ይህ ባህሪው የኢንጂነርነት ሙያን ለመቀላለል እንዳበቃው የተናገረው ከቴድኤክስ አዲስ መድረኮች በአንዱ ነበር።

ቴድኤክስ አዲስ እንደ እስራኤል ያሉ በንግግር ሰዎችን ማነሳሳት የሚችሉ ግለሰቦች ሀሳባቸውን የሚያካፍሉበት መድረክ ነው።
ተናጋሪዎች ወደ 20 ደቂቃ ገደማ ይሰጣቸዋል። ስለ ሙያዊ ህይወታቸው ያወሳሉ። እንዴት ውጣ ውረድን አልፈው ከስኬት ማማ እንደደረሱ ይናገራሉ። ተሞክሯችውን በማካፈል አድማጮችን ለማነሳሳትም ይሞክራሉ።
የእስራኤል ኢላማም ንግግሩን የሚሰሙትን ማጀገን ነበር። እሱ በመረጠው የሙያ መስክ የደረሰበትን መነሻ በማድረግ፤ ግብን ማወቅ ያላሰለሰ ጥርት ሲጨመርበት ውጤታማ እንደሚያደርግ ያመለክታል።
"ከቴድኤክስ አዲስ ተናጋሪዎች መሀከል ዩኒቨርስቲ እንኳን ሳይገባ ስልክ የሠራውን እስራኤል አልረሳውም" የሚለው የቴድኤክስ አዲስ ዋና አዘጋጅ ስንታየሁ ሰይፉ ነው።
የንግግር መድረኩን የጀመረው ማህበረሰቡ የስኬታማ ሰዎችን የህይወት ተሞክሮ በመስማት የ"ይቻላል" መንፈስ እንዲሰፍንበት መሆኑን ይናገራል።
የቴድቶክስ ታናሽ እህት ቴድኤክስ አዲስ
ስንታየሁ የቴድኤክስ አዲስ ሀሳብን የጠነሰሰው ከዘጠኝ ዓመት በፊት አየርላንድ ሳለ ነው።
አዳዲስ ሀሳብ የሚቀርብበትን የቴድቶክስ የንግግር መድረክ እንዲታደም በጓደኛው ይጋበዛል። ሳይንስን ለብዙሀኑ ተደራሽ የማድረግ ጽንሰ ሀሳብ የተስተጋባበት ንግግርም ያዳምጣል። በንግግሩ ስለተደመመ የቴድ መድረኮችን መከታተል ቀጠለ።
ቴድቶክስ ዓለም አቀፍ የንግግር መድረክ ነው። የቴክኖሎጂ፣ የመዝናኛና የዲዛይን ልሒቃን ወደ 20 ደቂቃ ገደማ ንግግር ያደርጋሉ።
ቴድቶክስ በተለያዩ ሀገሮች እህት ቅርንጫፍ ያለው ሲሆን የአዲስ አበባው ቴድኤክስ አዲስም ይገኝበታል።
"ብዙዎቻችን ውጪ ሀገር ጥሩ ነገር ስናይ ወደ ኢትዮጰያ መውሰድ እንፈልጋለን" የሚለው ስንታየሁ ቴድንም ወደ ኢትዯጰያ ለማሻገር የወሰነበትን ወቅት ይገልጻል።
ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት 45 ሰዎች ንግግር አድርገዋል። በሚታወቁበት የሙያ መስክ ያላቸውን ልምድ አካፍለዋል። ከሙያዊ ትንታኔ ባሻገር የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ምልከታቸውን አስደምጠዋል።
ቴድኤክስ አዲስ፤ በቴድቶክስ ህግጋት ለመተዳደር ተስማምቶ ፍቃድ ተሰጥቶቷል። ስምምነቱ በየዓመቱ የሚታደስ ሲሆን ታዳሚዎች የሚሰነዝሩት አስተያየት ከግምት ይገባል። በመድረኩ የማስታወቂያ፣ የፖለቲካና ሀይማኖታዊ ጉዳዮች አይስተናገዱም።
ቴድኤክስ አዲስImage copyrightTEDXADDIS
ተናጋሪዎቹ እነማን ናቸው?
ሰዎች በአንድ ንግግር ተአምራዊ ለውጥ ያመጣሉ ባይባልም የስኬት ታሪኮችን ማድመጥ አንዳች ብርታት እንደሚሰጥ እሙን ነው።
"ማህበረሰቡን ማነሳሳት የሚችሉ የቴክኖሎጂ፣ የመዝናኛና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ይቀርባሉ" ይላል ስንታየሁ።
ስኬታማ የሆኑ እንዲሁም መልካም ነገርን ማበርከት የሚችሉ ይጋበዛሉ። መድረክ ይሰጠን ብለው የሚጠይቁም አሉ። በታዳሚዎች የሚጠቆሙ ተናጋሪዎችም ይካተታሉ።
"ተናጋሪ ማግኘት ከባድ ነው። መጠነኛ ጉዳይን አግዝፈው መሸጥ የሚችሉ ተናጋሪዎች አሉ። ትልቅ ነገር ሰርተው ምንም መናገር የማይችሉም እንዲሁ" ሲል ተቃርኖውን ያስረዳል።
ከሀገር ውስጥ ባሻገር ከውጪ ያስመጧቸው ተናጋሪዎችን ይጠቅሳል። በእርግጥ የአቅም ውስንነት ስላለ አዘውትረው ከውጪ ለማስመጣት አይደፍሩም።
ስንታየሁ እንደሚለው በመድረኩ የሚጋበዙት ሰዎች ሀሳባቸውን በየትኛውም የህይወት ደረጃ ያለ ሰው እንዲገነዘበው ከሽነው ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
ስለቴድኤክስ የሚያውቁ ሰዎች በአዲስ አበባው መድረክ የመናገር እድል ሲያገኙ በደስታ ይቀበላሉ። እንዲከፈላቸው የሚጠይቁም አልታጡም። በቴድ ህግ መሰረት ለንግግር ገንዘብ መክፈል እንደማይፈቀድ የሚያወሳው ዋና አዘጋጁ፤ ባይከፈላቸውም ለመናገር የሚፈቅዱ ቢኖሩም ያለ ክፍያ አንዳችም ቃል አንተነፍስም ብለው ጥሪውን የማይቀበሉም እንዳሉ ያስረዳል።
የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቹ ንጉሡ አክሊሉ በቴድኤክስ አዲስ ንግግር ካደረጉ መካከል አንዱ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ባይቸረውም ባገኘው መድረክ ሀሳቡን ከማካፈል አይቦዝንም።
ቴድቶክስ አንጋፋ የንግግር መድረክ እንደመሆኑ በእህት ድርጅቱ ቴድኤክስ አዲስ ሀሳቡን እንዲያካፍል ሲጠየቅ እንደተደሰተ ያስታውሳል።
"አረንጓዴ ኢትዮጵያን መፍጠር ይቻላል?" የንግግሩ መነሻ ጥያቄ ነበር።
በተሰጠው አጭር ደቂቃ ሀሳቡን እያዋዛ ስለሚያቀርብበት መንገድ በቴድኤክስ አዲስ መምህራን ስልጠና ከወሰደ በኋላ ንግግሩን አቅርቧል።
"የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ እንደ ቅንጦት ይቆጠራል። የምዕራባዊያን ጉዳይ እንደሆነም ይታሰባል። ስለዚህ በተገኘው አጋጣሚ ስለ አካባቢጥበቃ እናገራለሁ" ይላል።
ንግግሩን ብዙዎች በማህበራዊ ድረ ገጾች ስለተጋሩት መወያያ ሆኖ ነበር። ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ መገኘቱ የሀሳቡን ተደራሽነት ያሰፋዋል። በሌላ በኩል በማህበራዊ ድረ ገጾች መነጋገሪያ የሚሆኑ ሀሳቦች ከአውድ የሚወጡበት ጊዜ እንዳለም ንጉሡ ሳይጠቅስ አላለፈም።
ንግግር ወዲህ እኛ ወዲያ?
ሀሳቦች የሚስተናገዱባቸው በቂ መድረኮች አሉ ወይ? የብዙዎች ጥያቄ ነው። በአደባባይ ሀሳብን የመግለጽ ተነሳሽነት ወይም ሀሳብ የሚንሸራሸርባቸው መድረኮችን የመታደም ፍላጎትስ አለ?
ለስንታየሁና ንጉሡ መልሱ "የለም!" ነው።
በተለይም የአደባባይ ንግግር በጣም አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ አይሞከርም። ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ጋር ሲነጻጸር ኢትዮጵያው ውስጥ ንግግር ቦታ መነፈጉ ጥያቄ ያጭራል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ 'ቶስትማስተርስ' ያሉ ንግግርን የሚያበረታቱ መርሀ ግብሮች ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ተስፋ ፈንጣቂ ቢሆኑም ከአዲስ አበባ ማለፍ ግን አልቻሉም።
ዘመኑ ተናግረው ማሳመን የሚችሉ ሰዎች ነው። ስለዚህም የንግግር ችሎታን ማስረጽ የግድ ይላል።
በስንታየሁ ገለጻ "የንግግር ባህል አልሰረጸም። ሀሳባችንን በመሸጥ ረገድም ክፍተት አለ። የአደባባይ ንግግር እንዲለመድ የውይይት መድረኮች መበራከት አለባቸው። መሰናዶዎቹም በዓመት አንዴና ሁለቴ ከመሆን ሊያልፉ ይገባል።"
ሀሳቡን የምትጋራው ቴድቶክስን ከሀገር ውጪ፤ ቴድኤክስ አዲስን ደግሞ በሀገሯ የታደመችው ቤተልሔም ናት።
"ሀሳባችንን እንዴት መሸጥ እንዳለብን አናውቅም። ጥሩ ነገር ቢሰሩም በአግባቡ ማብራራት ባለመቻል ብዙ እድል የሚያመልጣቸው በርካቶች ናቸው" ትላለች።
ቤተልሔም የታደመችው ኢትዮጵያዊ የደም ሀረግ ያለው እንግሊዛዊ ጸሀፊ ለምን ሲሳይ ንግግርን ነበር። ንግግር ካደረገ በኋላ ብዙዎች ጥያቄ በመሰንዘር መሳተፋቸው አስደስቷታል።
"ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያላቸው ሰዎችን ልምድ መስማት ይጠቅማል። በአንድ ቀን ንግግር ለውጥ ባይመጣም አስተሳሰብን ለመፈተሽና ሌላ ዕይታ ለመቃኘት ያግዛል። ከምንም ተነስቶ ትልቅ ደረጃ የደረሰ ሰው ተሞክሮ አነሳሽና ተስፋ ሰጪም ነው" ስትል የቴድ መድረኮች ምልከታዋን ታካፍላለች።
በተያያዥም መሰል መድረኮች የጥቂቶች መሆናቸውን በመጠቆም፤ ተደራሽነታቸውን የማስፋት ጉዳይን አዘጋጆቹ ያስቡበት ትላለች።
በቴድኤክስ አዲስ ከ250 እስከ 300 ሰው ይታደማል። ተሳታፊዎች ሲመረጡ የፆታ፣ የእድሜና የሙያ ስብጥርን ለመጠበቅ እንደሚሞከር ስንታየሁ ይገልጻል።
ንጉሡ በበኩሉ የንግግር መድረኮች አለመኖር ብዙሀኑን ለፅንፈኛነት እንዳጋለጠ ያምናል። "በሀገራችን ንግግር እንደ ሀጢያት ይቆጠራል። ሁላችንም ተገናኝተን ብንነጋገር ግን ከፅንፈኝነት ወደ መግባባት እንሸጋገራለን" ይላል።
ሀሳብና ሀሳብ መካከል ፍጭት ካልተደረገ ሁሉም በየፅንፉ የከረረ አቋም ይይዛል። የሀሳብ ልዩነትን ለማክበርም መነጋገሪያ መድረክ ያስፈልጋል።

No comments:

Post a Comment