Sunday, July 22, 2018

ባለፉት ቀናት በተከናወነ ኦፕሬሽን 10 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መያዙን ፖሊስ ገለፀ

ጥናትን መሰረት በማድረግ ባለፉት ጥቂት ቀናት በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጪ በተከናወነ ኦፕሬሽን በህገወጥ መንገድ የተያዘ 10 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መያዙን የፌደራል ፖሊስ ገለፀ።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ ጥናትን መሰረት በማድረግ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ፖሊስ በጋራ ባካሄዱት ኦፕሬሽን ነው የውጭ ሀገር ገንዘቡ የተያዘው።
በተጨማሪም 1 ሺህ በላይ የነብስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎች በዚህ ኦፕሬሽን መያዛቸውን ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።
ከነብስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎቹ መካከልም ሽጉጥና ጥይቶች እንዲሁም ሁለት መትረየሶች የሚገኙበት ሲሆን፥ 80 ሺህ የክላሽ እና የሽጉጥ ጥይቶችም መያዛቸውን ነው ያመለከቱት።
እነዚህ የጦር መሳሪያዎች በሱዳን እና በጅቡቲ በኩል የገቡ ስሪታቸውም በአብዛኛው ቱርክ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዋናነትም ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተደረገበት ዋና ዓላማ በሀገሪቱ ውስጥ አለመረጋጋትን መፍጠር ነው ብሎ ፖሊስ እንደሚያምንም ጠቁመዋል።
በህገወጥ መንገድ ተይዞ የተገኘውም የውጭ ሀገር ገንዘብ ሆነ ተብሎ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማዳከም የሚፈፀም ተግባር አካል እንደሆነም አንስተዋል።
በዚህ ተግባር የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ወደ ተግባር የሚቀየሩ ተጨማሪ ጥናቶች አሉ ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ፥ በሚቀጥሉት ሳምንታትም ይህ ኦፕሬሽን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

No comments:

Post a Comment