የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኤርትራ አቻው ጋር በነሐሴ ወር አጋማሽ አስመራ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ ሊያደርግ ነው።የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሁለቱን ሀገራት ወንድማማችነት ለማጠናከር አስመራ ከተማ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ባሳለፍነው ሳምንት ደብዳቤ መላኩ ይታወሳል።
የኤርትራ ብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ጥያቄውን መቀበሉን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ በመላክ ይሁንታውን ገልጿል።
ጨዋታውም የፊታችን ነሃሴ አጋማሽ ላይ አስመራ ከተማ የሚደረግ ሲሆን፥ የጨዋታው ትክክለኛ ቀን አዲሱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የሚወሰን ይሆናል ተብሏል።
ፌዴሬሽኑም መሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ለመፈፀም እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን ከሶከር ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በ1990 በተቀሰቀሰው የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ምክንያት የኢትዮጵያ ክለቦች እና ብሄራዊ ቡድኑ ከኤርትራ ክለቦች እና ብሔራዊ ቡድን ጋር ጨዋታ አድርገው አያውቁም።
አሁን በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረው ግንኙነት ወደ ሰላም በመመለሱ የኢትዮጵያ ክለቦች ከኤርትራ ክለቦች ጋር የእንጫወት ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛል።
ፋሲል ከነማ ጥያቄ አቅርቦ ከኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መልካም ምላሽ ያገኘ ሲሆን፥ የትግራይ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮም በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ጨዋታዎችን ለማድረግ ጥያቄ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጳጉሜን ወር ከሴራሊዮን ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን ያደርጋል።
ምንጭ፦ ሶከር ኢትዮጵያ
No comments:
Post a Comment