Tuesday, July 24, 2018

የቁንጅና ሚዛን


ቁንጅና እንደየማኅበረሰቡ ባህልና እሴት ሲያልፍም እንደ ዘመኑ የአስተሳሰብ ደረጃ ትርጉሙ ይለያያል፡፡ በአንድ ወቅት የቁንጅና ተምሳሌት የነበሩ ነገሮች ዘመን ሲለወጥ ትርጉማቸውም አብሮ ሲለወጥ ይስተዋላል፡፡ በየዘመናቱ በነበረው የሥልጣኔ ደረጃ የቁንጅና አረዳድ ሁኔታ ሰዎች ውብ ሆኖ ለመታየት ብዙ ነገሮችን ያደርጉም ነበር፡፡

በቁንጅና ታሪክ ከማይረሱ ፋሽኖች አንዱ በጥንታዊ ግሪኮች ዘንድ የውበት ምልክት ተደርጎ ይወሰድ የነበረው የተጋጠመ ቅንድብ አንዱ ነው፡፡ ቅንድቧ የተጋጠመላት ሴት ትልቅ የማስተዋል አቅም እንዳላት፣ የቁንጅና ቁንጮ ተደርጋ ትታሰብ ነበረና ፈላጊዎቿ ብዙ ነበሩ፡፡ ሴቶችም በቅንድቦቻቸው መካከል ያለውን ክፍተት በጥላሸትና በሌሎች ነገሮች ይሞሉት ነበር፡፡ አልፎ አልፎም ከቅንድባቸው የሚመሳሰል የፍየል ቆዳ ላይ ፀጉር ወስደው በቅንድቦቻቸው መካከል ያለውን ከፍተት ያጋጥሙም ነበር፡፡
‹‹የሴት ልጅ ውበቷ ግንባሯ ነው›› ብለው በሚያምኑ የመካከለኛው ዘመን ምዕራባውያን ዘንድ ደግሞ በተቃራኒው ቅንድብ የውበት አካል ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ ስለዚህም ሴቶቻቸው ግንባራቸው ጎልቶ እንዲታይ ሲሉ ቅንድባቸውን ሙልጨ አድርገው ያነሳሉ፡፡ ይበልጥ ቆንጅተው ለመታየት የሚሹ ሽቅርቅሮች ደግሞ ሽፋሽፍታቸውን ሳይቀር ብድግ ያደርጉታል፡፡ ከኢንደስትሪ አብዮት በፊት ደግሞ በፈረንሣይ የሴቶች የገረጣ ቆዳ የውበት ጥግ ነበር፡፡ ያለልክ የገረጣ ቆዳቸው ደም ሥራቸውን የሚያሳይ ከሆነ ደግሞ ቁንጅናዋ ምትሀታዊ ይሆን ነበረና ሴቶች ደምስሮቻቸውን በሰማያዊ ያቀልሙት ሁሉ ነበር፡፡
በቀይ ቀለም ከንፈርን ማስዋብ፣  ዓይንን በኩል ማስጌጥና ሌሎችም ቁንጅናን የሚያጎሉ መኳኳያዎችን መጠቀም ‹‹የሴተኛ አዳሪነት›› መለያ በነበረበት በንግሥት ቪክቶሪያ ዘመን ደግሞ የቁንጅና ትርጉም የተለየ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ የእንግሊዝ ሴቶችም ውኃ አጣጫቸውን ለማግኘት በራሳቸው መንገድ ቆንጆ ለመሆን ይጥራሉ፡፡ ከንፈራቸው ጽጌረዳ እንዲመስል ደጋመው ይነክሱታል፣ ጉንጫቸው ቀላ ብሎ እንዲያጓጓም ረዘም ላሉ ሰዓታት በቁንጥጫ ያደብኑታል፡፡
በአንድ ወቅት የጃፓን ሴቶች እውነተኛ ቁንጅና ከዳር እስከዳር የጠቆረ ጥርስ በነበረበት ጊዜም ጃፓናውያን ጥርስን ማጥቆር የሚችሉ የተለያዩ ውህዶችን እያዘጋጁ ይጨልጡ ነበር፡፡ ጥቁሩ ፈገግታዋ ለወንዱ ቀልቤ ወዶሃልና እንዴት ይሻሻላል? የሚል ጨዋዊ መልዕክት አለው፡፡ የደም ዝውውሩን እንዳቆመ  እንደ አስክሬን ሁሉ የነጣ ፊት የውበት መለኪያ ሆኖም ያውቃል፡፡ በየዘመኑ የሚቀያየሩትን የቁንጅና መሥፈርቶች ለማሟላት ተፈጥሮን ወደ አንድ የፋሽን አቅጣጫ እንድታዘነብል ብዙ ሰዎች የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ አቅጣጫዋን ስታ በየዘመናቱ ካሉ የቁንጅና መሥፈርት ጋር እንድትጣጣም ጎብጣለች፣ ቀንታለች፡፡ ሰዎች በዘመናቸው የነበሩ የቁንጅና መለኪያዎች ተሰፍረው ሚዛን ለመድፋት አደገኛ ኬሚካሎችን እስከ መጠጣት ደርሰዋል፡፡
ቆንጆ ሆኖ ለመታየት ከተፈጥሮ ጋር የሚደረገው ትግል አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው፡፡ ደርባባነት የሴትነት ጥግ የሆነበት ዘመን ሲያበቃ ክብደት ለመቀነስ የውፍረት መቀነሻ ውህዶችን የሚያሳድዱና ስፖርት ቤቶችን የሚያጣብቡ በዝተዋል፡፡ በአቋራጭ መንገድ ተሸናቅጠው መታየት የሚፈልጉና አቅሙ ያላቸው ቦርጫቸውን በኦፕራሲዮን ያስቀንሳሉ፣ ጉንጫቸው ከአጥንታቸው አልፎ እንዳይወጣ ሥጋቸውን ያስቆርጣሉ፣ ዕድሜ ያጨማደደውን ግንባራቸውን ያስወጥራሉ፣ ከንፈራቸው ድባድቦ ሆኖ ዕይታን እንዲስብ በኮስሞቲክስ ሰርጀሪ ያደልቡታል፡፡
በዘመናት መካከል የሚፈጠረው የቁንጅና መሥፈርት መለያየት እንዳለ ሆኖ በየባህሉ ያለው መለያየትም ሌላው ቁንጅናን እንደአተያዩ እንዲለያይ የሚያደረገው ነገር ነው፡፡ ከተሜዎች በባጊ ጂንስ፣ በቬል፣ በቃሪያ ሱሪና በሌሎች የፋሽን ዲዛይኖች ሲዘንጡ የሐመር ሰዎች ፀጉራቸውን በቀይ ጭቃ አቅልመው፣ ኃፍረታቸውን በእርፊ ጨርቅ ሸፍነው፣ አንገታቸውን በኮልኮሌ አስጊጠው፣ ወገባቸውን በብትራቸው ግርፊያ ተልትለው አምረው ይታያሉ፡፡ ለከተሜዎች እንከን የሆነው ጠባሳ ለሐመሮች የውበት አሻራ ነው፡፡ የተተለተለው ቆዳቸው ክፉ አጋጣሚ የተወላቸው ግድፈት ሳይሆን አይነግቡ የሚያደርጋቸው ጥበብ ነው፡፡
ውድ ውድ ልብሶችን ለብሶ በመዘነጥ ፈንታ ቆዳቸውን በተለያዩ ቀለማት ለሚያሳምሩት ሱርማዎች ቁንጅና መሥፈርቱ ሌላ ነው፡፡ ጆሮዋን እንደ ቋንጣ ተልትላ ለምትጌጠው የሱርማ ኮረዳ፣ ከንፈሯን ሰንጥቃ በለምቦጯ ውስጥ በምትከተው የምጣድ መጠን ለምትለካ የሱርማ ቆንጆ የውበት ሚዛን ፍፁም የተለየ ነው፡፡ እንሶስላ ሞቀው እግርና እጃቸውን ለሚያጠቁሩ የትግራይ ቆነጃጅቶች እንሶስላ ድምቀት ነው፡፡ ቀጫጨኑ አልያም ድርብርቡ ሹሩባቸው የውበታቸው ፈርጥ የሴትነት መለያቸው ነው፡፡ 
ባህሉን ጠብቆ ለቆየ የአፋር ወጣት ቁንጅናው ሲጨፍር እርግፍ እርግፍ የሚለው ዘንፋላ ፀጉሩ፣ እንደ በረዶ የነጣ ድርድር ጥርሱ፣ የሚያገለድመው ሽርጡ ላይ የሚሽጣት ጊሌው ነው፡፡ ለአይናፋሯ የአማራ ልጃ ገረድ ጌጧ ከአንገቷ ጀምሮ እስከ አይበሉባዋ የሚወርደው ንቅሳቷ ነው፡፡ በአንፃሩ ዘመናዊነት ለተጫናቸው ከተሜዎች ደግሞ ባህላዊ የቁንጅና መስፈርቶች ጊዜ ያለፈባቸው ፋሽኖች ናቸው፡፡
ንቅሳት በሺዎች የሚቆጠሩ ገንዘባቸውን አፍስሰው የሚያጠፉት ግድፈት ነው፡፡ እንስሲላ የማይታሰብ ነው፡፡ ከኋላ ቦፍ ብሎ የሚቀረው ቀጫጭን ሹሩባም ከስንት አንዴ የሚደረግ ነው፡፡ የከተሜዎች የቁንጅና መስፈርት ከምዕራባውያን የተቀዳና እንደ ወቅቱ የሚቀያየር፣ ታዋቂ ዲዛይነሮች፣ የሆሊውድ አክተሮች፣ ሜካፕ አርቲስቶችና የመሳሰሉት እንደፈለጉ የሚጠመዝዙት የውበት አዙሪት ነው፡፡ ሲላቸው ቁንጅና ልዩ ሆኖ መውጣት፣ ሲላቸው ደግሞ በተቃራኒው መረጋጋት፣ ደፋር መሆን ነው ይላሉ፡፡
ያለውን ተፈጥሯዊ ውበት በኮስሞቲክስ ማጉላት፣ የሌለውን መጨመር፣ የበዛውን መቀነስ፣ አጥንት የሚያስቆጥር ተክለ ሰውነት ባለቤት ሆኖ በአልባሳት መሽቀርቀር ዘመናዊው የቁንጅና ሚዛን የሚጠይቃቸው መሥፈርቶች ናቸው፡፡ እነዚህን መሥፈርቶች ለማሟላት ታዲያ እንደ ጥንቱና መካከለኛው ዘመን አልያም እንደ ባህላዊው የቁንጅና መሥፈርት ከባድ አይደለም፡፡ በዓመት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሰው የኮስሞቲክስ ኢንደስትሪ ሁሉን ነገር አልጋ በአልጋ አድርጎታል፡፡
እንደ አስፈላጊነቱ ባህላዊ መዋቢያዎችን ሁሉ ሳይቀር በቀላሉ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጎ እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ ሀር ነው ፀጉሯ ተብሎ የተዜመላትን ኢትዮጵያዊ ቆንጅት የሚያስከነዱ ፀጉሮች በያይነቱ እየተዘጋጁ ወደ ገበያው ይለቀቃሉ፡፡ አርቲፊሻሉን ከተፈጥሮ መለየት እስኪቸግር ሁሉንም የምርጥ ፀጉር ባለቤት የሚያደርጉ ረቂቅ ቴክኖሎጂዎች በሥራ ላይ ይውላሉ፡፡
‹‹ብዙ ዓይነት ፀጉሮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገቡት ከህንድና ከቻይና የሚገዙ ናቸው፡፡ እኛ ስንሸጥ የብራዚል፣ የጣልያን፣ የማሌዥያ እንላለን እንጂ ወደኛ አገር የሚገባው በብዛት ከህንድ ነው፤›› የሚለው የተለያዩ የመዋቢያ ግዓቶችን በተለይም ፀጉር መሸጫ ሱቅ ያለው ሮቤል ቀላቴ ነው፡፡ ከጉሬላ፣ ከፈረስ የሚቆረጡ ከሴንቴቲክ ነገሮች የሚዘጋጁ የፀጉር ዓይነቶች ገበያውን አጥለቅልቀውታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለምንም ችግር እንደ ኮፍያ የሚጠለቁ ሒውማን ሄሮች በገፍ ገበያ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ፀጉር ላይ የሚሰፉ በፍሪዝ መልክ የተዘጋጁም እንዲሁ በብዛት ይገኛሉ፡፡ ጭንቅላታቸው ስፌት መቀበል ለማይችል ለምሳሌ የካንሰር ታማሚ ለሆኑ የተዘጋጀ አናታቸው ላይ የሚለጠፍም የፀጉር ዓይነት አለ፡፡ ‹‹እስከ ፈለጉት ድረስ መቆየት ይችላል፡፡ ማስነሳት ሲፈልጉ ሪሙቨር (ፀጉር ሙልጭ አድርጎ የሚያነሳ ኬሚካል) በመጠቀም ነው፤›› የሚለው ሮቤል ይህንን ዓይነቱን ዊግ በብዛት የሚጠቀሙት ጥቁር አሜሪካውያኖች መሆናቸውን ይናገራል፡፡
ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑት የፀጉር ብራንዶች 300 ብር ጀምሮ እስከ 8,000 ባለው ዋጋ እንደሚሸጥ ይናገራል፡፡ ሹሩባ ተሠርተው የተዘጋጁ እንደ ኮፍያ የሚጠለቁ ሁሉ አሉ፡፡ የተለያዩ ባህላዊ አሠራርን መሠረት አድርገው የተሠሩትን ሹሩባዎች እስከ ሦስት ዓመት ድረስ መጠቀም እንደሚቻል ሮቤል ይናገራል፡፡ እንደሥራቸው 1,300 ብር እስከ 2,000 ብር ድረስ ይሸጣሉ፡፡
በቀን እስከ 100 የሚሆኑ ደንበኞችን እንደሚያስተናግድ የሚናገረው ሮቤል ደንበኞቹ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ወንዶችም ናቸው፡፡ ራሰ በራ የሆኑ ወንዶች ለሠርግ፣ ለምርቃትና ለሌሎችም ፕሮግራሞች በሚስጥር ወደ ሮቤል ጎራ ይላሉ፡፡ ‹‹ሒውማን ሄር መቀጠላቸውን የሚያውቀው ባለሙያ እንጂ ሌላ ሰው በቀላሉ ሊለያቸው አይችልም፤›› ይላል፡፡ በድብቅ ወደ ሱቁ ጎራ የሚሉት የወንዶች ደንበኞቹ ቁጥር ቀላል አለመሆኑን ይናገራል፡፡
ውበትን ያጎላሉ ተብለው ከሚዘወተሩ መዋቢያ ግብዓቶች ሌላው ዓይንን በኩልና በተለያዩ ቀለማት ማስዋብ ነው፡፡ ይህ በሜካፕ አርቲስቶች ዘንድ ራሱን የቻለ ሳይንስ ነው፡፡ የትኛው ቀለም ከየትኛው የሚለውን ብቻ ሳይሆን ከሥር የሚቀባውንና ከላይ የሚደረብውንም ለይቶ ማወቅ ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ የዓይኖቿ ሽፋሽፍት ወፍ ያሳርፋል የሚባለውን ያህል የተጋነነ ባይሆንም ረዘምዘም ያለ ሽፋሽፍት እንዲኖራት ይጠበቃል፡፡ ለዚህም በማስካራ ማቅለም የተለመደ ሲሆን፣ አለፍ ሲልም አርተፊሻል ሽፋሽፍቶችን የመሰካት ነገር በብዛት ይታያል፡፡
‹‹ሴንቴቲክ፣ ስሪ የሚባሉና ሌሎችም የተለያየ ዓይነት ሽፋሽፍቶች አሉ፡፡ ስሪ ፀሐይ ላይ ያንፀባርቃል፡፡ ማጣበቂያ ሳያስፈልገው በራሱ ስክት የሚል ማግኔት ሽፋሽፍትም አለ፤›› በማለት አማራጮቹ በዙ መሆናቸውን ይናገራል፡፡
ወገቧ ስምንት ቁጥር፣ መቀመጫዋ ሰፊ፣ ጡቷ እንደ ቀስት የተወደረ፣ ፀጉሯ ደግሞ ዝንፍልፍል ሲሆን፣ በቁንጅና መሥፈርት ተመዝና አትወድቅም፡፡ ቀጥ ያለ አፍንጫ፣ ጎላጎላ ያሉ ዓይኖችና ዳጎስ ያለ ከንፈር ሲታከልባት ደግሞ ቁንጅናዋ መነጋገሪያ ያደርጋታል፡፡ ፈላጊዎቿ ሊበዙ፣ የቁንጅና መለኪያም ልትሆን ትችላለች፡፡ እንዲህ ማኅበረሰቡ የተስማባቸውን የቁንጅና መሥፈርቶች አሟልቶ መገኘት ለበርካቶች አይታደሉትም፡፡ ነገር ግን መሥፈርቶቹን አሟልቶ ቆንጆ መስሎ መታየት የሚቻልባቸው መንገዶች በዚያው መጠን ብዙ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት መቀመጫን ለማስፋት እንደ ሆሊውድ አክተርሶች ታዋቂ የቀዶ ሐኪም ዘንድ መሄድ ሳያስፈልግ ሰፊ መቀመጫ ካላቸው እኩል መታየት ይቻላል፡፡ ገነት (ስሟ ተቀይሯል) ዳሌዋ ከሱሪ ውስጥ ሙልት ብሎ እንዲታይ ያስቻለውን ባለ እስፖንጅ ፓንት ማድረግ ከጀመረች ቆይታለች፡፡ በመጀመርያ አካባቢ ለሠርግና ለአንዳንድ ፕሮግራሞች ሲኖሩባት ነበር የምትለብሰው፡፡ እየቆየች ግን በማንኛውም ቀን መልበስ ሥራዬ አለችና አረፈችው፡፡ ለነገሩ መቀመጫዋ ሰፊ ከመሰለላት በኋላ ሰው እሷን የሚያይበት ሁኔታም ተቀይሯል፡፡ ለክፉ አይሰጥም የሚባል ዓይነት ዳሌዋ ዳጎስ ብሎ ከቀሚስ ወስጥ ሞንደል ምንደል ሲል እሷም ወዳዋለች፡፡ ሌሎች ሴት ጓደኞቿም የዚህ ጉደኛ ፓንት ተጠቃሚ ቢሆኑም እንደሷ ግን ሁሌ እንደማያደርጉ ትናገራለች፡፡
ጡቶቿ በልብስ ውስጥ ጎልተው እንዲወጡ የሚያደርጉ ባለ እስፖንጅ ጡት ማስያዣም ታደርጋለች፡፡ ባለ አንድ፣ ባለ ሁለት እስፖንጅ ተብለው የሚሸጡ ጡት ማስያዣዎችን መጠቀም የጀመረችው ልብስ ያሳምራል በሚል ነበር፡፡ አንድ ሁለቴ ካደረገች በኋላ ግን እንደ ፓንቱ ሁሉ ካለሱ አይሆንም አለች፡፡ በፊት የምትጠቀማቸውን ዓይነት ጡት ማስያዣዎች ዞርም ብላ አታያቸውም፡፡ ለነገሩ እስፖንጅ የሌላቸውን ጡት ማስያዣዎች ፈልጎ ማግኘትም ከባድ ነው፡፡ ሱቆችን አጨናንቀው የሚገኙት እነዚህ ሙቀታቸው ለጡት ካንሰርና ለተለያዩ የጤና ጠንቆች እንደሚያጋልጡ የሚነገርላው ባለስፖንጅ ጡት ማስያዣዎች ናቸው፡፡
‹‹የጨርቅ ጡት ማስያዣዎችን የሚጠቀሙት ትልልቅ ሰዎች ናቸው፡፡ አሁን እኮ ብዙም ገበያ ላይ የሉም፤›› የምትለው ሃያ ሁለት መስመር ላይ የተለያዩ አልባሳት መሸጫ ሱቅ ያላት ሚላይ ተሾመ ነች፡፡ ከጣልያን፣ ከዱባይና ከአሜሪካ ከምታስመጣቸው ዕቃዎች መካከል የተለያዩ የመዋቢያ ግብዓቶች አሉ፡፡ በመስታወት መደርደሪያዋ ውስጥ ከሚታዩ አልባሳት መካከል ጡት ማስያዣዎች ቢኖሩም አንዱም ግን ስፖንጅ አልባ አይደሉም፡፡ ለነገሩ ስፖንጅ የሌላቸው ጡት ማስያዣዎች ጠያቂ ስለማይኖራቸው መያዙ ጥቅም የለውም፡፡
‹‹እስከ 30 ሺሕ ብር ድረስ የሚሸጥ ሒውማን ሄር አለ፡፡ አምስት ዓመት ድረስ ይጠቀሙታል፡፡ በመሀል ግን ከለር መቀየር ሲፈልጉ ወይም ቁመቱን ማሳጠር ሲፈልጉ ሌላ ጨምረው ይገዛሉ፤›› የምትለው ሚላይ ፀጉሯ ደህና የሚባል ቢሆንም ሒውማን ሄር ከመቀጠል ግን አልቦዘነችም፡፡ ቁንጅና ይጨምራሉ ተብለው ከተዘጋጁ የመዋቢያ ግብዓቶች ሌላው ጥፍር ነው፡፡ ሴቶች ለሠርግና ለሌሎች ፕሮግራሞች ቄንጠኛውን አርተፊሻል ጥፍር በጥፍራቸው ላይ ያስለጥፋሉ፡፡ እስከ 150 ብር የሚሸጠው ጥፍር በመደበኛነት የሚጠቀሙም ብዙ መሆናውን ሚላይ ትናገራለች፡፡
አፍጥጦ የሚወጣን ቦርጭ እንዳይታይ የሚያደርግ ወቅታዊውን የቁንጅና መሥፈርት አሟልተው ተሸናቅጠው እንዲታዩ የሚያደርግ ባንዴጅ ነገርም እንዲሁ በገፍ ገበያ ላይ ከሚወጡ የመዋቢያ ግብዓቶች አንዱ ነው፡፡ ቁመትን የሚጨምሩ የተለያዩ ዓይነት ታኮ ጫማዎችም በዚህ ረገድ መነሳት ይችላሉ፡፡
ወቅቱን እየጠበቀ ለሚቀያየረው የቁንጅና ትርጉም በርካቶች እጅ ይሰጣሉ፡፡ መሥፈርቱን አሟልቶ ቆንጆ ሆኖ ለመታየት ብዙ ነገሮችን ያደርጋሉ፡፡ አሳዛኙ እውነታ ግን ባላቸው ተፈጥሯዊ መልክ ቆንጆ የሚባሉ ሳይቀሩ የአርተፊሻል ገበያውን መጋፋታቸው ነው፡፡ ‹‹ዊግ የተዘጋጀው ፀጉር ለሌላቸው ቢሆንም ዊግ መጠቀም የሚብሰው ጥሩ ፀጉር ባላቸው ነው፤›› ይላል ሮቤልም፡፡ ዘንካታ ቁመት ያላቸው ሳይቀሩ ቁመት ከፍ የሚያደርጉ ታኮ ጫማዎች ላይ መሰቀል ሥራዬ ያሉ ብዙ ናቸው፡፡ እንደ ሁኔታዎች የሚቀያየረውን የቁንጅና መሥፈርት ተከትሎ ከመባዘን፣ ለሰዎች አድናቆት ጆሮ ከመስጠት ቆንጆ ነኝ ብሎ ማመኑ በቂ ይመስላል፡፡


No comments:

Post a Comment