Tuesday, July 24, 2018

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሕክምና ከየት እስከ የት



በባህላዊ የሕክምና ጥበብ ድልድይ ተሻግሮ ለተዓምር የቀረቡ ፈውሶችን መስጠት የቻለው ዘመናዊ ሕክምና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ቆይቶ ነበር፡፡ ጉንፋን ሲይዘው ዳማከሴ ጨምቆ፣ አላስቆም አላስቀምጥ ለሚለው ጥርሱ ስራስር ነክሶ፣ ለሚያዋክበው ቁርጠት ጤና አዳም ጨምቆ፣ ክፉ መንፈስ ተጠናወተኝ ሲል በየሃይማኖቱ ፀልዮ፣ ድኝ ታጥኖ ሌላም ድንገተኛና አጣዳፊ ሕመም ሲያጋጥመው ቅጠል መበጠስ ለሚቀናው የኅብረተሰብ ዘመናዊ ሕክምና ብዙም አንገብጋቢ ጉዳይም አልነበረም፡፡
አንዳንድ ምዕራባውያን የሕክምና ባለሙያዎች በተለያየ ተልዕኮ ወደ ኢትዮጵያ በመጡባቸው ወቅቶች ሕመምተኞችን ያክሙ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ዘመናዊ ሕክምና በተደራጀ መልኩ አገልግሎት የጀመረው ግን በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በዓድዋ ጦርነት የቆሰሉ አርበኞችን ለማከም ሲባል ነበር፡፡
በጦርነቱ የተጎዱ ኢትየጵያውያንን ለመርዳት በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ባህር የተሻገሩ የሩሲያ ቀይ መስቀል አባላት ነበሩ፡፡ ሰባት ሐኪሞች፣ 12 ነርሶችና አንድ ፋርማሲስት ያለው የሕክምና ቡድኑ ሐምሌ 1888 .. አዲስ አበባ ገባ፡፡ ከአገራቸው ጭነው ያመጡትን ድንኳን ጥለው የቆሰሉትን ወደ ማከሙ ተግባር የገቡት ጊዜ ሳያጠፉ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ዘመናዊ ሕክምና ለኢትዮጵያውያን ሲተዋወቅ አስፈላጊነቱም የማያጠያየቅ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡
ችግሩ ዘመናዊ ትምህርት የራቀው እረፍና ጨብጦ ከሞፈር ሲታገል የሚውለው፣ ከዓለማዊ ሕይወቱ ይልቅ መንፈሳዊነት ያመዝንበት ለነበረው የዚያ ዘመን ነዋሪ ሐኪም መሆን ተዓምር እንጂ ዕውን የማይሆን ለነጮች ብቻ የታደለ ችሎታ ያህል የማይታሰብ ነገር ነበር፡፡
ቅጠል መበጠስ የጥቁር ኪኒን ሰቶ ራስ ምታትን ማስታገስ ደግሞ የነጮች እንደሆነ ይታመን በነበረበት በዚያ ወቅት ነገሥታቱን ያክሙ የነበሩ ነጭ የሕክምና ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ወቅት ነበር የሦስት ዓመት ሕፃን ሳሉ በኮለኔል ቻርለስ ቻምበርሊን ወደ ህንድ ተወስደው የነበሩት ወርቅነህ እሸቴ ሐኪም ሆነው የኢትዮጵያን ሕዝብ ያስደመሙት፡፡ ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የገዛ ሽጉጣቸውን ጠጥተው መቅደላ ላይ በወደቁበት በዚያች ቀውጢ ሰዓት ነበር ከእንግሊዙ ወታደር ቻርለስ ጋር የተገናኙት፡፡ በጦርነቱ ከወላጆቻቸው ተነጥለው ሲያለቅሱ የተገኙት ወርቅነህ ወደ ህንድ ተወሰዱ፡፡
የመቅደላው ትርምስ ወርቅነህ ህንድ ሄደው ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩና ለአፍሪካውያን የማይታሰብ የሚመስለውን የሕክምና ሙያ ባለቤት እንዲሆኑ መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡ የሕክምና ትምህርታቸውን ከፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ ሲያጠናቅቁ፣ እንግሊዝ ከሚገኘው ግላስኮ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በቀዶ ሕክምና ሙያ የክብር ተመራቂ ነበሩ፡፡ በወቅቱ የነበረው የእንግሊዝ ሐኪሞች ማኅበር ‹‹የመጀመርያው ባለ አንጎል ጥቁር ሐኪም›› የሚል የምስክር ወረቀት ሰጥተዋቸውም እንደነበር የሕክምና ጥበብ ኢትዮጵያ በሚል የተጠናቀረው የዶክተር ጋሻው አረጋ ጽሑፍ ያሳያል፡፡
በኢትዮጵያ የሕክምና ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጁ ባለሙያ ሐኪም ወርቅነህ በእንግሊዝ ግዛት ሥር በነበረችው በርማ ቀዶ ሐኪም ሆነው ሠርተዋል፡፡ የሐኪሙን ዝና የሰሙት ዳግማዊ ምኒልክም ዶክተሩ አገራቸው ተመልሰው ወገኖቻቸውን እንዲያገለግሉ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር ተጻጽፈው 36 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ሐኪም አዲስ አበባ እንዲገቡ ሆነ፡፡ ለዘመናዊ ሕክምና እንግድነት ይሰማቸው ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ሙያውን ወርሶ የአገር ልጅ በአገር እጅ ማድረግ የማይታሰብ ነበርና ለሕክምና አገልግሎቱ ታሰቦ የተሠራ የቅድመ ዝግጅት ሥራ አልነበረም፡፡
ሐኪም ወርቅነህ አዲስ አበባ ሲገቡ ሕክምና የሚሰጥበት አንድ ክፍል ስንኳ አልተዘጋጀም ነበርና ዳስ ጥለው ነበር ሕክምና መስጠት የጀመሩት፡፡ ኢትዮጵያዊው ሐኪም በዳሳቸው ውስጥ የሚሠሩት ተዓምር ሰዎችን ከሞት አፋፍ፣ ለዓመታት ካሰቃያቸው ደዌ፣ ከአጣዳፊ ሕመምና ከክፉ ቁስል ማትረፍ መቻሉ ሲረጋገጥ ነበር ከዳስ ተላቀው መደበኛ የሕክምና መስጫ እንዲገነባ የሆነው፡፡
የሆስፒታሉ ግንባታም መጋቢት 7 ቀን 1890 .. ተጀመረ፡፡ ክረምት ገባ ተብሎ ግንባታው ሳይቋረጥ፣ የውጭ ምንዛሪ ጠፋ ተብሎ ሒደቱ ሳይዳከም የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ግንባታ በቶሎ ተጠናቀቀ፡፡ ሆስፒታሉ ሥራ በጀመረ በመጀመርያው ዓመትም 8,378 ሰዎችን ማከም ቻለ፡፡ 153 ሰዎች ኦፕራሲዮኖች ተደረጉ፣ 3,602 ሰዎች ደግሞ ከሆስፒታሉ መድኃኒት ወሰዱ፡፡ በዚህ መልኩ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሕክምና ዳዴ ማለት ሲጀምር ሐኪም ወርቅነህ በነጮች በመታገዝ ብዙ አድርገዋል፡፡ የአፄ ምኒልክ ሐኪም የነበሩትን ሙሴሀር ማኒየርን ተክተው ሠርተዋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አክመዋል፣ የሕክምና ትምህርትም አስተምረዋል፣ ሲያልፍም በርካቶች በራሳቸው እንዲያምኑና ፈለጋቸውን እንዲከተሉ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡
የጤና ጉዳይ አንድ ሁለት እያለ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ራሱን ችሎ እንዲወጣ ተደረገ፡፡ እንደ ንግዱ፣ እንደ ገንዘቡ ዘርፍ ሁሉ 1948 .. የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተቋቋመ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ባለሙያዎቹን እዚሁ ለማፍራት ተንደረደሩ፡፡ 1964 .. የአዲስ አበባ የሕክምና ፋኩልቲ በሕክምና ዘርፍ በልዕልት ፀሓይ ሆስፒታል በአሁኑ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ስድስት ተማሪዎችን ማስተማር ጀመረ፡፡ ተማሪዎቹ ከፊሎቹን የትምህርት ዓይነቶች ባህር ማዶ ሄደው ተምረው የመጡ ነበሩና ተመርቆ ወደ ሥራ ለመግባት ብዙ አልወሰደባቸውም፡፡ በሰኔ 1960 .. አምስቱ ሐኪሞች ተመረቁ፡፡ ባህር ማዶ ሄደው ለመከታተል የሚገደዱባቸውን ከፊሎቹን የትምህርት ዓይነቶች ሙሉ በሙሉ እዚሁ መስጠት የሚቻልበት አቅም መገንባትም ተቻለ፡፡
ዛሬ ላይ የደረሰው ዘመናዊ የሕክምና ጥበብ ውስብስብ የሚባሉ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶች የሚሰጡበት፣ ከዓመታት በፊት በአገር ውስጥ ሐኪሞችና መሣሪያ ደፍሮ ለማከም ከባድ መስለው ይታዩ የነበሩ የሕክምና ዓይነቶች መስጠት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ በዚህ ረገድ ለበርካቶች ዕፎይታ መስጠት የቻለውን የልብ ቀዶ ሕክምናን ማንሳት ይቻላል፡፡ እንደ ልብ ተሯሩጠውና ቦርቀው ለመጫወት ያልታደሉ የልብ ሕመም ያለባቸውን ታዳጊዎች በአገር ውስጥ የማከም አቅም መፍጠር ከተቻለ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡  
ቀደም ሲል ያጠራቀሙትን ጥሪት አሟጦ ቤት ንብረት ሽጦ ለሕክምና ባህር ማዶ መውጣት ግድ ይል ነበር፡፡ በተሠሩ የዘመቻ ሥራዎች አስፈለጋጊውን መሣሪያና ብቁ ባለሙያዎችን እዚሁ መፍጠር በመቻሉ ሕፃናትን ለማሳካም የነበረው እንግልት እንዲቀር ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህን ለሕፃናት ብቻ ተብሎ የተፈጠረውን አገልግሎት ወደ አዋቂዎች የማድረስ ሥራም ተጀምሯል፡፡ በዚህ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑ ታካሚዎች መካከል የመጀመርያዋ ወይዘሪት ትዕግሥት ኃይሉ ነች፡፡
ትዕግሥት የልብ ሕመም እንዳለባት ያወቀችው ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ልቧ መደበኛው የሆነውን ደም የማጣራት ተግባሩን በሚገባ መከወን እንዳይችል ከሚያደርገው እንከን ጋር ነበር የተወለደችው፡፡ ‹‹ልቤ ላይ ቀዳዳ ነበር፡፡ ስለዚህ የተጣራው ደም ካልተጣራው እየተቀላቀለ ችግር ይፈጥርብኛል፤›› የምትለው ትዕግሥት ቀጥታ ለሕመም ባይዳርጋትም እንደ ጉንፋን ያሉ ቀላል ሕመሞችን አስታኮ ድክምክም እንድትል ያደርጋት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ሕመሟ በአንድ ጊዜ የአልጋ ቁራኛ ባያደርጋትም ውሎ እያደረ የከፋ ችግር ውስጥ እንደሚከታት እርግጥ ነበረና ያሳስባት ነበር፡፡ በመጀመርያ አካባቢ ያለባት ችግር በትክክል ምን እንደሆነ ማወቅም ቀላል አልነበረም፡፡ የተለያዩ ባለሙያዎች የነገሯት የምርመራ ውጤት የተለያየም ነበር፡፡ ችግሯ በልቧ ላይ ያለው ቀዳዳ መሆኑ ከተረጋገጠም በኋላ ምንም ነገር ማድረግ አልቻለችም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሕክምናው በአገር ውስጥ አይሰጥም፣ ውጭ ሄዶ ለመታከምም አቅሟ አይፈቅድም ነበር፡፡
እንደ እሷ ዓይነት ውስብስብ የጤና ችግር ያለበት እያንዳንዱ ደቂቃ ባለፈ መጠን ወደ ሞት እየተጠጋ መሆኑ ደጋግሞ ይሰማዋልና የሚያድርበትን ጭንቀት የተሸናፊነት ስሜት መገመት አይከብድም፡፡ አድፍጦ ከሚጠብቃት ሞት መላቀቅ የቻለችው ‹‹በእኛ አገር አይሠራም፤›› ብለው የነገሯት የልብ ቀዶ ሕክምና መጀመሩን ስታውቅ ነበር፡፡ ዓመታት ካስጨነቃት ሕመም ለመገላገል ሦስት ሰዓት ብቻ ነበር የፈጀባት፡፡
የማይሳካ ይመስል የነበረው የኩላሊት ንቅለ ተከላም አንዱ የኢትዮጵያ ሕክምና ዘርፍ እመርታ ነው ኩላሊታቸው ሥራ ያቆመ ብዙዎች ኩላሊታቸውን ተክቶ ደም የሚያጣራ የዲያሌሲስ ማሽን ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈሉ ሕይወታቸውን ያቆያሉ፡፡ በሳምንት እስከ አራት ጊዜ የሚታዘዝላቸውን ዲያለሲስ ለአንድ ጊዜ ብቻ እስከ 2,000 ብር ድረስ እየከፈሉ ይጠቀሙም ነበር፡፡ አንድ ዲያለሲስ አድፍጦ የሚጠብቃቸውን ሞት በአንድ ቀን እንደማራቅ ያህል ነው፡፡ በዚህ የአልሞት ባይ ተጋዳይነት የሕይወት ትንቅንቅ ውስጥ በርካቶች ተስፋ ቆርጠው ሞትን መርጠዋል፣ የተደላደለ ኑሮ የነበራቸው ቤት ንብረታቸውን ሸጠዋል ሌላም ብዙ ነገር መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ በፊት በውጭ አገሮች ብቻ የሚሰጥ የነበረው ይህንን ሰቆቃ የሚያስቀርላቸው የንቅለ ተከላ ሕክምና በአገር ውስጥ ባለሙያ መስጠት ተችሏል፡፡ ሕክምናው በተጀመረ አካባቢ 50 ለሚሆኑ ታማሚዎች የንቅለ ተከላ ሕክምና ማድረግም ተችሏል፡፡
ከእነዚህ የሕክምና ትሩፋቶች ጀርባ ያሉ በሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ፈር ቀዳጅነት የሙያው ባለቤት መሆን የቻሉ ሐኪሞች የትውልድ ባለውለታ ናቸው፡፡ ሐኪምነት ከማልቀስ ውጪ ምናቸውን እንዳመማቸው መናገር የማይችሉ ሕፃናትን፣ በደረሰበት አደጋ ራሱን የሳተ የድንገተኛ ክፍል ታካሚ፣ በቃሬዛ ተንጋለው፣ በአንቡላንስ ተጣድፈው ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውስጥ ሆነው ተዋክበው የሚያዋክቡ ሕመምተኞችን ሕመማቸውን አውቆ ፈውስ መስጠት ልዩ ጥበብ ነው፡፡  ሐኪምነት ሥራ ብቻ ሳይሆን እንደ ዋዛ የሰዎችን ነፍስ ይዞ ፈትለክ ለማለት ከሚጣደፈው ጊዜ ጋር ግብግብ መፍጠር፣ ሞት አፋፍ የደረሱ ታካሚዎችን ሕይወት በትንሹ መቀጠል ነው፡፡ ሐኪም መሆን ክቡሩን የሰው ልጅ ሕይወት ለማዳን መመረጥም ነው፡፡ የሐኪሞች ሕይወት የማያባራ የሰዎችን ጭንቀት እያዩ አብሮ መጨነቅ መረበሽ የሚበዛውና በሩጫ የተሞላ ነው፡፡ የማዳኑ ሩጫ ዝናን ከማትረፍ ያለፈ ትርጉም የሚሰጠው፣ ማዳን ሽንፈትን ማሸነፍ፣ ጊዜን ድል መንሳት፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የመኖር ምክንያት መሆን ነው፡፡ ወዲህ በምግብ እጥረት የተጎዱን ወዲያ ደግሞ አለገደብ በልቶ ለውስብስብ የጤና ችግሮች የተዳረጉ ወገኖች እኩል  የሚስተናገዱበት የተቃርኖ መድረክም ነው፡፡ ሕክምና ሞት አድፍጦ ከሚጠብቃቸው ሰዎች ጋር መተዋወቅ መግባባትም ሊሆን ይችላል፡፡ ያልጠበቁት ታካሚ ዓይኑ እያየ ሞቶ ማዘንና ከራስ መጣላትም ነው፡፡
‹‹ሞት ለሁላችንም የማይቀር ነገር ቢሆንም ለአንድ ሐኪም ትልቁ ሐዘን የሚያክመው ታካሚ ሲሞት ነው፡፡ ሳይጠበቅ ድንገት ሲሞቱ ደግሞ በጣም ውስጥሽ ያዝናል፡፡ ትጎጃለሽ፡፡ መትረፍ እየቻለ ሰው ሲሞት ሐኪሙም በትንሽ በትንሹ ውስጡ ይሞታል፡፡ በዚህ የተነሳ ሥራ መሥራት የሚያቅታቸው፣ ድብርት ውስጥ የሚገቡ ወጣት ሐኪሞች ብዙ ናቸው፡፡ እኛ እንኳ በጊዜ ሒደት ተላምደነዋል፤›› ያሉት / ገመቺስ ማሞ የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንትና የውስጥ ደዌ ሐኪም ናቸው፡፡ 
/ ገመቺስ በሙያው 31 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ በጎንደር ክፍለ አገር በፎገራ አውራጃ ቆላድባ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ ጤና ጣቢያ ነበር ሥራ የጀመሩት፡፡ ለጤና ጣቢያው የመጀመርያ ሐኪም ሆነው እንደተመደቡ ያስታውሳሉ፡፡ በቆላድባ ወረዳ ጤና ጣቢያ የጀመሩት የሕክምና ጉዞ በኢትዮጵያ የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አድርሷቸዋል፡፡ በእነዚህ የሙያ ጉዞዎችና የሥራ ዓመታት ብዙ ገጠመኞችን አስተናግደዋል፡፡ በርካቶችን አክመዋልም፡፡ እስካሁን ምን ያህል ሰዎች ማከማቸውን ‹‹በትንሹ በቀን 30 ሰው አያለሁ፣ በሳምንት ስድስት ቀናት እሠራለሁ፡፡ ታምሜ ካልቀረሁ በስተቀር ከሥራ ቀርቼ አላውቅም፡፡ እንግዲህ 30 31 ዓመት ማባዛት ነው›› አሉ እንደ ማሰብ ብለው፡፡ 
እንደ ዶክተር ገመቺስ ላሉ ሐኪሞች ታካሚዎችን ሊያሳዝን የሚችል የምርመራ ውጤት መግለጽ በራሱ ሌላ ፈተና ነው፡፡ የመዳን ተስፋ ይኖረኝ ይሆን ብሎ ከፊቱ የሚታይን ጭላንጭል ተስፋ እፍ ብሎ ማጥፋት ማንስ ይደፍራል፡፡ በተለይ በሽታቸው ዕድሜ ልካቸውን እንደ ጥላ የሚከተላቸው ዓይነት ጭንቀቱ ከባድ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ዶክተር ገመቺስ ‹‹ከታካሚዬ ጋር አብሬ አልቅሼ አውቃለሁ›› ሲሉ ለታካሚው የማይድን በሽታ እንደያዘው መግለጽ ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደ አሁኑ ደግሞ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ወሳኝ የሆኑ መድኃኒቶች በሚጠፉበት ጊዜ ይህንን ግዛ ብሎ ማዘዣ መጻፍ ሌላው ፈተና ይሆናል፡፡ ‹‹በቀላሉ ማከም እየቻልን ለታካሚው የምንጽፈው መድኃኒት ጠፍቶን እንጨነቃለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መድኃኒቱ ስላለ ብቻም ማዘዝ አይቻልም፡፡ ታካሚው መግዛት ይችላል ወይ የሚለውንም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብለን ጽፈን ብንሰጠው ዋጋውን ይጠይቅና ይቅርብኝ ብሎ ሂዶ ዳማከሴውን ይወስዳል፤›› ሲሉ ለሐኪሙ በአገር ውስጥ ያለውን የመድኃኒት አቅርቦት፣ የታካሚውን የመግዛት አቅም ማገናዘብ ሌላ ሥራ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከተሻገረ ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የዘመናዊ ሕክምና ጥበብ እንደ / ገመቺስ ያሉ ሐኪሞችን ማፍራት ችሏል፡፡ ሐኪሞችን በአገር ውስጥ አስተምሮ ማስመረቅ 1968 .. የተጀመረ ቢሆንም እስከ 2009 .. ድረስ 5,303 አጠቃላይ ሐኪሞች፣ 1,552 ስፔሻሊስትና 234 ሰብ ስፔሻሊስት ያደረጉ በድምሩ 7,089 የዘለለ ቁጥር ያላቸው ሐኪሞችን ማፍራት እንዳልተቻለ / ጋሻው ባቀረቡት ጽሑፍ አሳይተዋል፡፡
2010 .. የመጀመርያ ሩብ ድረስ 28 በላይ የመንግሥትና ስድስት የግል ሪፈራልና ማስተማሪያ ኮሌጆች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣ ከእነዚህም 13 የሕክምና ትምህርትን ቢሰጡም አሁንም ከባድ የሰው ኃይል እጥረት ይስተዋላል፡፡
አንድ ሐኪም በቀን በትንሹ እስከ 30 ሰዎችን የማየት ኃላፊነት አለበት፡፡ ካለው የአገልግሎት ፍላጎት አንፃር ይህም በቂ የሚባል አለመሆኑን በረዥም ቀጠሮ የሚመላለሱ ታካሚዎችን ማየት በቂ ነው፡፡ ሆስፒታሎች ወሳኝ የሆኑ መገልገያ መሣሪያዎች በምን ያህል መጠን ያገኛሉ? የሚለው ጉዳይም አጠያያቂ ነው፡፡ አገር ውስጥ ባሉ ባለሙያዎችና መሣሪያ መሠራት አይቻልም በሚል ውጭ አገር ሄዶ ለመታከም የሚገደዱ ብዙ ናቸው፡፡
‹‹ለሕክምና አገልግሎት ወሳኝ ብለን ካነሳናቸው ነገሮች አንዱ ጥራት ያለው የሕክምና ትምህርት ነው፡፡ የተንሻፈፈ ትምህርት የተማረ ሐኪም በቂ የሆነ አገልግሎት መስጠት አይችልም፡፡ ዝም ብሎ ፎቅ ስለተሠራ ብቻ ሆስፒታል አይሆንም፡፡ በውስጡ አስፈላጊው የሰው ኃይልና መገልገያ ቁሳቁስ መኖር ግድ ነው፡፡ የግብአት ችግር ሐኪሙን እጀ ሰባራ ያደርጋል፤›› በማለት / ገመቺስ ጥራት ያለው ሕክምና ለሕዝቡ ለማድረስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ፡፡    


No comments:

Post a Comment