አቶ
መላኩ ፈንታ፣ የቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር
የዛሬው
የቆይታ አምድ እንግዳ አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው፡፡ የ50 ዓመት ጎልማሳው አቶ መላኩ ከ1981 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2005 ድረስ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ከጀማሪ ኤክስፐርትነት እስከ ሚኒስትርነት ባሉ ኃላፊነቶች ከመሥራታቸው በተጨማሪ፣ በሠሩባቸውና በመሯቸው ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ በማምጣት የተመሠከረላቸው ናቸው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን በሚኒስትር ማዕረግ በዋና ዳይሬክተርነት መምራታቸው ይታወሳል፡፡ ከ2005 ዓ.ም. ግንቦት ወር ጀምሮ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረውና ክስ ተመሥርቶባቸው ለአምስት ዓመታት እስከ ግንቦት ወር 2010 ዓ.ም. ድረስ ታስረው ቆይተዋል፡፡ በቂ መረጃ ሳይሰበስብ ከሁለት ወይም ከሦስት ክሶች መብለጥ የሌለባቸውን ክሶች አብዝቶ በመክሰስ ዜጎችን ለእስር መዳረግ ተገቢ አለመሆኑን፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ ዜጎች ያለ ወንጀላቸው በወንጀል ተፈርጀው መታሰራቸው የፖለቲካ ምኅዳሩን ከማጥበብና ሰላምን ከማደፍረስ የዘለለ ሚና እንደሌለው መንግሥት ገልጾ፣ የበርካታ እስረኞች ክስ እንዲቋረጥና በይቅርታ እንዲፈቱ ሲያደርግ ለመጨረሻ የቅጣት ውሳኔ የተቀጠሩት አቶ መላኩም ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ተፈትተዋል፡፡ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት የሆኑትን አቶ መላኩ በትምህርት፣ በሥራ፣ በእስር ስላሳለፏቸው ጊዜያትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከሪፖርተር
ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን እንሆ።